nvmn

Spread the love

የቤንች ሸኮ ዞን ገቢዎች መምሪያ ከስር መዋቅሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በበጀት አመቱ ዕቅድ አሰባሰብ ዙሪያ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በመድረኩ የተሳተፉ አካላት እንደተናገሩት የገቢ ሴክተር ከፍተኛ የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ከሚስተዋልባቸው ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም መነሻ በዘርፉ የታክስ ማጭበርበርና ስወራ ፣ የግብር ከፋይ ቁጥር ቅሸባ ፣ ሀሰተኛ ደረሰኞች ማዘጋጀትን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ ብለዋል።

በከተሞች የተጨማሪ እሴት ታክስ ፣ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የአከራይ ተከራይ ግብር ፣ በገጠር የገጠር መሬት መጠቀሚያና የገጠር ኢንቨስትመንት መሬት ግብር ክፍያ አሁንም ችግር ውስጥ ያሉ ዘርፎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

የመረጃ አያያዝና ጥራት ችግር ፣ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ጋር ተያይዞ በኮሚቴ ከተሰራው ይልቅ ወደ ተቋም ወስዶ በውሳኔ ለማስከፈል መሞከር ፣ ሽያጫቸው የደረጃ ሆኖ ሳለ የግብር ከፋይ ደረጃቸውን ዝቅ አድርጎ መመዝገብ ፣ ከቤት ሽያጭ ጋር ተያይዞ ዝቅ አድርጎ ውል ማቅረብ እንዲሁም የህግ ማስከበርና የቅንጅት ስራው ደካማ መሆን አሁንም የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸው ተገልጿል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የግብርና ፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት በየመዋቅሩ ያሉንን ሀብቶች በተገቢው አውቆ መምራትና የገቢ አሰባሰብ ስራችን ላይ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

አመራሩ የተሰጠውን የህዝብና የመንግስት ኃላፊነትና አደራ በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ወረዳዎች ከብድር ሊወጡ ይገባል ያሉት አቶ መስፍን የኢኮኖሚ ፖተንሺያሎችን መለየትና በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። የድጋፍና የቅንጅት ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ኃላፊው የገጠር መሬትና የኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ በጥብቅ ዲሲፕሊን ገቢው ሊሰበሰብ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተረፈ ስንቡል እንደተናገሩት ባለፉት አመታት ከአዲሱ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጋር በቅርበት በመተጋገዝ እየተሰራ ነው ብለዋል። በቀጣይም የነጋዴዎች መረጃ ፣ የደረጃ ሽግግር ፣ የግብር አከፋፈል ፣ የባለሙያ ስነ ምግባር ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። የተቋሙን አሰራርና የመረጃ አያያዝ ማዘመንና ፈጣን አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል።

የታክስ ስወራ ፣ ማጭበርበር ፣ ሀሰተኛ ደረሰኞች እና በዚህ ተግባር የሚሳተፉ ባለሙያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ የማስወሰድ ስራ ተጠናክሮ ይሰራል ብለዋል። የተሻሻለው የገጠር መሬት መጠቀሚያ አዋጅ በፍጥነት ወደ ስራ ሊገባ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ወንዱ ታደሰ እንደተናገሩት የታክስ ስወራና ማጭበርበር በስውር የሚካሄድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በጥብቅ ሊመራ ይገባል ብለዋል። የጋራ ገቢና ፒኤልሲዎች ጋር ተያይዞ መረጃዎችን በተገቢው ማጥራትና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *