
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን የእስካሁን ታሪኩንና የወደፊት ተልዕኮውን በሚመጥን መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) አስታወቁ።
ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ የዩኒቨርሲቲውን የራስ ገዝነት የሪፎርም አፈጻጸም እና የ75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ አከበባርን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወጣው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በቅቷል ብለዋል።
ከመስከረም 2016 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የሽግግር ስራ አመራር ቡድን በማዋቀር በራስ ገዝነት እሳቤ ላለፉት 18 ወራት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመቅረጽ እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በራሱ መስፈርትና ምዘና ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪ የሆኑና በየዘርፉ ጉልህ ሚና እየተወጡ የሚገኙ ከ280ሺህ በላይ ምሩቃንን ያበረከተ አንጋፋ የትምህርት ተቋም መሆኑን አስረድተዋል።
የዩኒቨርሲቲው 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል “ያለፈውን በመዘከር መጪውን በማለም” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበርም አስታውቀዋል።
የአልማዝ ኢዮ ቤልዩ ክብረ በዓል ዝግጅትን እስከ ታህሳስ 30/2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ከሁሉም ኮሌጆችና የምርምር ኢንስቲትዩቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በክብረ በዓሉ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስና ሴሚናሮች፣ የቀድሞ ምሩቃን ሳምንት፣ የ75 ዓመታት ጉዞ ዶክመንታሪ፣ የህትመት ውጤት፣ የሥነ-ጥበብና ኪነ-ጥበብ እንዲሁም ስፖርታዊ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ አብራርተዋል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሚል ስያሜ በታህሳስ 1943 ዓ.ም የተመሰረተው የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በራስ-ገዝ የአስተዳደር ሥርዓት አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ነፃነቱን ጠብቆ እየሠራ የሚገኝ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
