




በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሄራዊ ደህንነት ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀንአ ያደታ (ዶ/ር) የተመራ የክትትልና ድጋፍ ቡድን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አጠቃላይ የኮሙኒኬሽን ስራዎች ዙሪያ ዛሬ ምልከታ አድርጓል።
ቡድኑ ከአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋርም ተወያይቷል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፥ ስለ ተቋሙ አሁናዊ የስራ ክንውንና በቀጣይ ለመተግበር የታቀዱ የኮሙኒኬሽን ስራዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ አገልግሎቱ ዓላማ ተኮር የሆነና ህዝብን ማዕከል ያደረገ የኮሙኒኬሽን ስራዎችን በማደራጀት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ የሰላም፣ የልማትና ዲሞክራሲ መረጃዎች ትክክለኛና አሁናዊ ገጽታቸዉን ይዞ ለህዝብ እንዲደርሱ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ትክክለኛና ወቅታዊ የይዘት መረጃዎችን ለሚዲያ ተቋማት ማቅረብና መምራት፣ የሚዲያ ክትትልና ዳሰሳ ማድረግ፣የፌዴራልና ክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማትን ማስተባበር የአገልግሎቱ ዋና ተግባራት መሆናቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
በዚህም በውጤት የታጀቡ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የሚዲያ ዘገባዎች ከሁሉ በላይ በሰላም ግንባታ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና የሁሉንም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንቅስቃሴን በማሳየትና የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ ከማድረግ አኳያ በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል።
በቀጣይ የሚዲያ ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ እንደሚከናወንም በመጠቆም።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ምህዳር እና የኮሙኒኬሽን አግባቦች ጥራት በማሳደግ ትክክለኛ፣ፈጣንና ቀጣይነት ያለዉ የመንግስት መረጃዎች ፍሰታቸዉን ጠብቀዉ የህዝብ ተጠቃሚነትን እንዲያረጋግጡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሚና የላቀ መሆኑ ተመላክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ክትትልና ድጋፍ ቡድን አባላት የአገልግሎቱን የስራ እንቅስቃሴ መመልከታቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
