የተነደፉ ኢኒሼቲቮችን ከውጤት ለማድረስ አመራሩና ባለሙያው በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል፦ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

Spread the love

በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት እና በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ዘርፎች ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የዛሬውን መድረክ ሲያጠቃልሉ የግብርና ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ተጠያቂነትን ያሰፈነ አሰራር መከተል ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዘርፉም ተፈጥሮንና የሰውን አቅም በመጠቀም ይበልጥ ለውጤታማነት መትጋት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሌማት ትሩፋት ስራዎች የተሰጠውን ትኩረት ያህል ውጤት ሊመዘገብ እንዳልተቻለም ተናግረዋል ።

በሌማት ትሩፋት ስራዎች እዚህም እዚያም ያለው ውጤት የሚያኩራራ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ወራት ስታንዳርዱን በጠበቀ መንገድ ዘርፉን መደገፍ ይገባልም ብለዋል።

በክልሉ በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ዘርፍ እሴት የሚጨምሩ አሰራሮችን ለመተግበር እንዲያስችልም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም ውጤታማነት የኢንዱስትሪ ሼዶችን ለመገንባት መሬት የመለየት ስራ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የግብርናውን ልማት ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችልም በክልሉ የተነደፉ ኢኒሼቲቮችን ከውጤት ለማድረስ አመራሩና ባለሙያው በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።

እየተደረገ ባለው የግብርና ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠልና በቀጣይ በሚሰሩ ኢኒሼቲቮች ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ መመሪያና አቅጣጫዎችንም ሰጥተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በሰጡት ማብራሪያ የግብርናው ዘርፍ በመደማመጥና በመግባባት ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በቀሪ ወራቶች የሚሰሩ የግብርና ልማት ስራዎች በክልሉ የተነደፉ የ3 ዓመት ኢኒሼቲቮችን ለማሳካት መንደርደሪያ የሚሆኑ ናቸው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሌማት ትሩፋት ስራዎች ያሉ ጅምር አሰራሮችን ከውጤት ለማድረስ በስታንዳርድ መሠረት መተግበር ይኖርበታል ብለዋል።

በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ሊሰሩ ይገባል ያሉት አቶ ማስረሻ የግብርና ልማት ሰራተኛውን ክህሎት ይበልጥ ለማጎልበት ስልጠናዎችን አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

በእንስሳትና ዓሳ ሀብት እንዲሁም በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ተሳታፊዎች አስተያየቶችን አክለውበታል።

በሌማት ትሩፋት ስራዎች ያለው ጅምር ስራ የሚበረታታ ቢሆንም በስታንዳርድ ከመምራት አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በወተትና እንቁላል ምርት ማሻሻያ ላይም ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ።

ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ምርታማነትን ለመጨመር አሁን የተነደፈውን ኢኒሼቲቭ ከግብ ለማድረስ ተግተው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አሁን ላይ ያለውን ጅምር ስራዎች አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ክልላዊ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት፣ስርጭትና ዕዳ አመላለስ ሰነድ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አማካሪና የጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ ዮሐንስ መላኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *