አዲሱ ትውልድ የአድዋን ድል በእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ፣ በልማትና ድህነትን ድል በማድረግ ሊደግም ይገባል ፦አቶ ፋጂዮ ሳፒ

Spread the love

129ኛው የአድዋ ድል በዓል መታሰቢያ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር አድዋ ኢትዮጵያን በአንድነት ፣ በህብረትና በጀግንነት ታሪክ የሰሩበትና መላው አፍሪካን ነጻ ያወጡበት የድል በዓል ነው ብለዋል።

አድዋ ለጥቁር የአፍሪካ ህዝቦች የነጻነትና የኩራት በዓል ነው ያሉት አቶ ፋጂዎ አዲሱ ትውልድም የአድዋን ድል እውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትን በመላበስ ፣ ኢትዮጵያዊነትን በማጽናት ፣ በልማትና ድህነትን ድል በማድረግ ሊደግሙ ይገባል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች በዛብህ በመድረኩ እንደተናገሩት አድዋ የበርሊን የአፍሪካን ቅርምት የሰበረ ፣ የጣሊያንን ወራሪ ሀይል አሳፍሮ የመለሰ የጥቁር ህዝቦች የድል በዓል ነው ብለዋል።

አድዋ የውጫሌን የማጭበርበር ሴራ ያፈረሰ ፣ ቆራጥ የሀገራችን መሪዎች ለህዝባቸው የክተት ጥሪ በማድረግ በአንድነትና በጀግንነት ታሪክ የሰሩበትና ለአለም ህዝቦች ጀግንነትን ያወጁበት ነው ብለዋል። እስከ አፉ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር በጦር ፣ በጎራዴና ጋሻ በጀግንነትና በጥበብ ተዋግተው በጠላት ያልተገዛችና ያልተንበረከከች ሀገርን አውርሰውናል ብለዋል።

አዲሱ ትውልድም ከፋፋይና ነጣጣይ ትርክትን በገዢና ብሔራዊነት ትርክት በመተካት ኢትዮጵያዊነትን ማጽናትና ማዝለቅ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች በዛብህ “አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል ለውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም አድዋና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉና የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ናቸው ብለዋል። አድዋን ምሳሌ በማድረግ አባቶች ያስረከቡንን ነጻ ሀገር በሰላም ፣ ልማትና ድህነትን ታሪክ በማድረግ አደራቸውን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጅዎ ሳፒ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ዛሬ ላይ የሀገራችንን ሰንደቅ ከፍ አድርገን የምንሰቅለው በቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች ሀገር ስላለችን ነው ብለዋል።

በቅኝ አለመገዛታችን የተሟላ ወኔ ፣ ስነልቦና እና ልበ ሙሉ አድርጎናል ብለዋል። ይህን እንደ ዕድል በመጠቀም ሁሉ አቀፍ ሰላም ፣ ልማትና ዲሞክራሲን በማስፋት ውጤታማ መሆን ይገባል ብለዋል። በመንደር ፣ ጎሳና በሰፈር መከፋፈል ትተን እንደ ሀገር አንድ ሆነን ድህነት ላይ መዝመትና ድል ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸዉን የዘገበዉ የቤንች ሸኮ ዞን የመንግሰት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *