




129ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል!” በሚል መርህ ቃል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉን በሚመለከት በቀረበው ፓናል ውይይት ሀሳብ የሰጡት የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ለውጥ በማረጋገጥ የአድዋ ድልን በትውልድ ውስጥ ማጽናት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አድዋ የመደማመጥና የመከባበር እንዲሁም በአንድነት የመቆም ውጤት መሆኑን የጠቆሙት የመድረኩ ተሳታፊዎች የአሁኑ ትውልድ፥ በህዝቦች መካከል አንድነት ከሚሸረሽሩ ነጠላ ትራክቶች በመራቅ ልዩነቶችን በንግግርና ውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር አለበት ብለዋል።
አድዋ በደምና ላብ የተገኘ አንጸባራቂ ድል መሆኑን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ የዛሬው ትውልድ ጠንክሮ በመስራት ደህንነትና ኃላቀሪት ላይ ድል በመቀዳጀት ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ በምግብ ራሷን የቻለች ሀገር የማድረግ ኃላፊነት እንደተጣለበት በአጽንኦት ተናግረዋል።
የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፌ-ጉባኤ አቶ ግርማ ደፋር በበኩላቸው ውስጣዊ አንድነት በማጠናከር ከደህንነት ለመላቀቅ መትጋት አለብን ብለዋል።
አፌ-ጉባኤው አክለው የአድዋ ድልን ለማጽናት ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ በታማኝነትና በቅንነት ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በቁርጠኝነት ማገልገል እንዳለበትም ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድ የራሱን አድዋ በልማትና ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ መቀዳጀት እንደሚጠበቅበት የገለጹት የክልሉ የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በሁሉም መስክ በጋራ በመቆም አሸናፊነት መጎናጸፍ ይገባል ብለዋል።
አድዋ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆኑን በጽናት ያሳየ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ደማቅ ታሪክ መሆኑን የተናገሩት አቶ አንድነት ዛሬም በተለያየ መልኩ የሚስተዋለውን ኢ-ፍትሀዊነት እና መድሎን በመቃወም ለእኩልነት መቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
