


ታሪካዊው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን ለመላው ጥቁር ሕዝብ የኩራት ምንጭ እንድትሆን ያደረገ ሕያው ድል ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
129ኛ የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ዕሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።
የሴንተር ኦፍ ግሎባል አፍሪካ መስራችና ዋና ዳይሬክተር እዝራ አሃሮን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛችና የጥቁር ህዝብና የአፍሪካውያንን የነጻነት ብርሃን የፈነጠቀች ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ያስመዘገበችሁ ድል የጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ጥልቅ መነሳሳትን የፈጠረ የኩራት ምንጭና የነጻነት ቀንዲል መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም መላው የዓለም ጥቁር ህዝቦች ኢትዮጵያን እንደ ምልክት የማየትና ጥብቅ ግንኙነት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
የታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ ሼህ ኢሳ ሙፍቲህ ዑመር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን እና ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትዕምርት ናት።
ቀደምት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ሉዓላዊነት ሳይደፈር ተከብሮ እንዲቆይ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን የአፍሪካውያንና የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክትና የኩራት ምንጭ አድርጓታል ነው ያሉት።
ዓድዋ ኢትዮጵያውያን በኅብር ሆነው ያሳኩት ሕያው ድል መሆኑን ገልጸው፤ የታሪክ ተመራማሪዎች የጀግኖቹን ገድል በመሰነድ ለትውልዱ የማሳወቅና የማስተማር ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሼህ ኢሳ አክለውም ወጣቶችም የቀደምት ኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በመውረስ ለሀገራቸው ብልፅግና መትጋት አለባቸው ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
