ለሕብረተሰብ ጥቅም በሚሰሩ የልማት ስራዎች ሁሉም ትብብር ሊያደርግ ይገባል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

Spread the love

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።

ለማህበረሰብ ጥቅም ከሚሰሩ ልማቶች በተጨማሪ የኢንቨስትመንት የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው፤ እንደ ቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ መብራት ኃይል፣ አየር መንገድ፣ የልማት ስራ በሚሰሩበት ወቅት 100 በመቶ ካሳ ይከፍላሉ ብለዋል።

ነገር ግን ካሳ የሚጠየቅበት መንገድ ለምን ዓላማ? የሚለውን በደንብ ማለየት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ለመስራት ሃብት ከተለያዩ ቦታዎች ሲገኝ ለካሳ የሚጠየቀው ገንዘብ ስራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

መሰረተ ልማት እንዲሟላ ሲጠየቅ ዋና ተጠቃሚው ማሕበረሰቡ እንደሆነ በመገንዘብ መሰረተ ልማቶችን ለመስራት የሚያስፈልግ ሀብት ሲገኝ ክልሎች ደግሞ ቦታ ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ የልማት ስራዎችን ለመስራት ሀብት ሲገኝ የሚጠየቀው ካሳ ከልማት ስራው በላይ እንደሆነ አንስተዋል።

የካሳ ጉዳይ በአንዳንድ አካባቢዎች የልማት ስራዎች እንዳይከናወኑ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ከዚህም አልፎ የመዝርፊያ ስልት እየሆነ ምምጣቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ልማት ለማምጣት አለመቻሉን እና ልማት ከተጀመረ በኋላ በካሳ ምክንያት የልማት ስራዎች እንደሚቋረጡ ገልጸው፤ ይህንንም ለመከላከል ሕግ ማውጣት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ለማሕበረሰቡ በሚሰራ ፕሮጀክቶች ሁሉም አካል ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *