












እንደምን ቆያችሁን ውድ አምባቢዎቻችን? ባለፉት ተከታታይ ወራት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ? በሚል አምዳችን የስድስቱ የዞኖቻችንን ጠቀለል ያለ እይታ በወፍ በረር ማስቃኘታችን ይታወቃል።
ከእነዚህም ስለ ዳውሮ ዞን ባስቃኘናችሁ ክፍል በዳውሮ ዞን ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊና የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲሁም የዳውሮ ብሔረሰብ ከሚታወቁባቸው ባህላዊ ዕሴቶች ዋና ዋናዎችን አቀርበን ነበር። ዛሬ ደግሞ ከነዚህ ባህላዊ ትውፊቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ባህላዊ የፍትህ ስርዓት “ዱቡሻ ዎጋ”ን መርጠን ለውድ አንባቢያን እነሆ ብለናል።
የዳውሮ ብሔረሰብ የተለያዩ ክዋኔዎችና ትውፊቶች እንዲሁም የባህል ዕሴቶች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል። ከነዚህም አንዱ ባህላዊ የግጭት አፈታትና የፍትህ ስርዓት የሆነውን የማህበረሰቡ ከቀደምንት አባቶች ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው “የዱቡሻ” ስርዓት ነው።
የዳውሮ ብሔረሰብ አባቶች ከጥንት ጀምረው በዱቡሻ ዎጋ ባህላዊ የፍትህና የግጭት አፈታት ስርዓትን ደንግገው ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፤ ዛሬም ይህን ባህላዊ ስርዓት በማከናወን በርካታ ችግሮችን እየፈቱ ይገኛሉ፡፡
ይህ የዳውሮ ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ከብሔረሰቡ ባህላዊ የፖለቲካ ስርዓት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን እንደ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት ዕድገትና ሂደት የዳኝነት ስርዓቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመነደገ እንደመጣ በስፋት ይነገርለታል።
በዳውሮ ማህበረሰብ የበደለ የሚጠየቅበት፤ የተበደለ የሚካስበት ባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ስርዓት የሚካሄድበት ቦታው ዱቡሻ ይባላል። ይህ ያጠፋ ሰው የሚጠየቅበትና በግልፅ የአደባባይ ችሎት የሚዳኝበት “ዱቡሻ” የሚከናወነው ትልቅ ዛፍ ካለበት ሰፊ ሜዳ ላይ ነው ።
ደቡሻ በአብዘኛው በሜዳማ አካባቢ ለውሳኔ አሰጣጥና ለስርዓቱ ማስከጃ የሚሆኑ እንደዋርካ፣ ዝግባና ሾላ የመሳሰሉ ትላልቅ ዛፎች ስር ችሎት ይካሄዳል፤ ከዋርካውና ዝግባው ትልቅነትና ግርማ ሞገስ የተነሳ ራሳቸው የሚያስፈሩና ውሳኔ የሚሰጡ የሚመስሉ ናቸው። በሁሉም ዳውሮ አካባቢዎች የችሎት አደባባዮች ወይም “ዱቡሻዎች” ያሉ ሲሆን ዱቡሻዎች ከባህላዊ የዳኝነት ስርዓት አገልግሎት በተጨማሪ ለሎችም ሕዝባዊ ስብሰባዎች ያገለግላሉ።
በዳውሮ ብሔረሰብ ሕዝቡ ያጎለበተውን ሰናይ ዕሴቶች በመተላለፍ ፍትህን ያጓደለ፣ የሰረቀ፣ ደካማውን የበደለ፣ ገንዘብ ተበድሮ የካደ(እምነት ያጎደለ) እና በሌላው ላይ ክፋትን የፈፀመ ሁሉ በዱቡሻ አደባባይ በሕዝብ ፊት በዕድሜ በገዘፉ፣ በሕይወት ልምዳቸው በከበሩ የሀገር ሽማግሌዎች ፊት ያስቆማል። እናም በዱቡሻ አደባባይ ላለመቆምና በማህበረሰቡ የቅጣት ስርዓት ላለመግባት ሁሉም የራሱን ጥንቃቄ ያደርጋል። ብሔረሰቡ ወግና ባህል የተወሰነና የተገደበ የቅጣት መቀጫ ወይም ካሣ ስርዓት ባይቀመጥም በዕደሜ በገፉ ከየጎሣው በተወከሉ ሽማግለዎች ፊት መቆሙ፣ እምብተኛ ከሆነ በማህበራዊ ህይወት መገለሉና በሀሰት ከማለ ባህላዊ ማላ እስከ ልጅ ልጅ ይተላለፋል ተብሎ ስለሚፈራ ሂደቱን ከባድ ያደርገዋል።
በዱቡሻ የክስ አቀራረብና ክርክር ሂደቱ እንደ ዘመናዊ ዳኝነት በጽሁፍና በተጻፈ ህግ ላይ ተመስርቶ ሳሆን በባህላዊ ሁኔታ በአፍ/በንግግር ከትውልድ ወደ ትውልድ ስወርድ ሲዋረድ በመጣ መንገድ ቢሆንም ግን እንደ ዘመናዊ ዳኝነት የግራ ቀኙ ክርክር ከተሰማ በኃላ ጊዜ ካልበቃም በተለዋጭ ቀጠሮ ማስረጃ የሚደመጥበት ሥርዓት ነው።
ለውሳኔ አሰጣጥ ከ3 የዳውሮ ጎሳዎች ማላ፣ ዶጋላ እና አማራ የተወጣጡ ሽማግሌዎች ተመራርጠው ይቀመጣሉ። እነዚህ ሽማግሌዎች በከሳሹና ተከሳሹ ወገን ስምምነት የሚመረጡ ሲሆኑ በዱቡሻ የአቀማመጥ ስርዓትም ከዛፍ ስር ከላይ በኩል ባህላዊ ዳኞች ከታች በኩል ከሳሽና ተከሳሽ ይቀመጣሉ። ለሽምግልና የሚመጡ ሰዎች ካሳራ/አንካሴና ጭራን በመያዝ ጋቢ ለብሰው ከብደውና ግርማ ሞገስ ተላብሶ ይቀመጣሉ።
በዱቡሻ የሚሰጥ ውሳኔ በበዳይና ተበዳይ መካከል እርቄ ሠላም የሚያወርድ እንጂ ለበቀል የሚያነሳሳ ባለመሆኑ ግጭትን ለመቀነስ ፋይዳው የላቀ ነው። ስለሆነም በዳይ በሚቀጣበት ወቅት የሚሰጠው የውሳኔ ቅጣት ለእግዚአብሔር ይቅር ተባብሎ እንዲኖሩ የሚያደርግ፣ ትንሽ ቅጣት ቢጣል እንኳን ለዱቡሻ ወግና በቀጣይ ተመሣሣይ ጥፋት አጠፍቶ እንዳይገኝ ለማስተማር ነው እንጂ ካሣ መብላትን ብዙም የማይደግፍ እንዲሁም የተቆረጠና የተገደበ የካሣ አከፋፈል መጠን የሌለው፤ ለእስራት የማይዳርግ እንዲሁም በፍ/ቤትና በፖሊስ ጣቢያ የሚባክነው ወጪ፣ ጊዜና ጉልበትን የሚቀንስ በመሆኑ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያለው የዳኝነት ስርዓት ነው ዱቡሻ።
የዱቡሻ ስርዓት የባህላዊ ዳኝነትና ግጭት አፈታት ብቻ የሚካሄድበት ሳይሆን የተደበቁ ወንጀሎች “በኦቲያ” (አውጫጭኝ) ስርዓት የሚወጡበት፣ የውሸት ክሶች ቀርበው በመሐላ የሚጣሩበት (የመሀላ ቁሳቁሶች ጉቶ እንጨት፣ ጭድ የቀርከሃ ልባስ (ጳሻ)) በማቅረብ በመሃላ እውነት የሚወጣበትም ነው፡፡
በዱቡሻ ስረዓት የታረቁ ሰዎች ደግም ወደ ግጭት እንዳይሄዱ በገበተ ውሃ ተሞልቶ ብቅልና የሴት እንሴት ኮባና እርጥብ ሳርና ዛንዛ በመያዝ ከዛሬ ጀምሮ እሮቄ ሠላም ስላወረድን ወደ ኃላ አናይም በጋራ እንኖራለን በሚል ቃል መሐላ ስለሚፈጽሙ ጉዳዩ ዳግም አይነሳም ።
የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን በሚመለከት በመጀመሪያ በአካባቢው በሚገኘው (በባይራ) ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ቅር የተሰኘው ወገን፣ ወደ “ቶካ ባይራ” (በእድር ደረጃ ያሉ) ይግባኝ በማቅረብ በተመረጡ ሽማግሌዎች ጉዳዩ ታይቶ ይወሰናል፡፡ አሁንም በተሰጠው ውሳኔ ያልረካ ወገን “ለቦልቦላ ባይራ” (ምን ማለት ነው) ያቀርባሉ፣ በዚህ ሁሉ ቅር የተሰኘው አንደገና ጉዳዩን በይግባኝ ወደ “ቶላ ጋምባላ” (ንጉሡ ችሎት) በመውሰድ ያስወስናል፡፡ የ”ቶላ ጋምባላ” ውሳኔ ይግባኝ የሌለው የመጨረሻ ውሳኔ በመሆኑ ባይስማማም የመቀበል ግዴታ አለበት።
የዱቡሻ ውሳኔ ላይ ቅሬታ አቀራረብ ስርዓትን በተመለከተ ከሳሽና ተከሳሽ ወይም ተበዳዩንና በዳዩን የነጠላ/ጋቢ ጫፍና ጫፍን በማሰር ወደሚቀጥለው የፍርድ ሂደት ይግባኝ ይዞ ይሄዳሉ። ነገር ግን በዱቡሻ ባህላዊ ዳኝነት ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት ብቃት ያለውን ማስረጃ ማግኘት ወሳኝ በመሆኑ የይግባኝ ጥያቄና የውሳኔ የመሻር ሂደት እምብዛን አይደለም።
ነገር ግን የተለያዩ የዱቡሻ ችሎቶችን አልፎ የተሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ የማይቀበልና የሚያስቸግር ግለሰብ ካለ እንዲቆጠቡ ለማድረግ “ቦሁዋ” ስርዓት ይገለላል። ይህ ሰው ለአካባቢውም ለህዝብም አይጠቅምም ተብሎ ስለሚታሰብ፤ ያን ጊዜ የከሳሽም ሆነ ተከሳሽ (በዳይም ሆነ ተበዳይ) ዘመዶች ተሰብስበው ከህዝብ ወጥተህ የት ትሄዳለ በሚል የማግባባት ስራ ይሰራሉ።
ሌላው በዳውሮ ብሔረሰብ ዘንድ ከመደበኛው የዳኝነት ስርዓት በተጨማሪ አንድ ወንጀል ማንነቱ ባልታወቀ ሰው ተፈፅሞ ሲገኝ በአከባቢው ባለው መሪ ትዕዛዝ መለከት ወይም በዳውሮኛ “ሎኮዋ” ተነፍቶ ሕዝብ ሁሉ ወደ ባህላዊ የመሰብሰቢያ ስፍራ (ዱቡሻ) እንዲወጣና እንድሰበስብ ይደረጋል። በዚህ ጥሪ መሠረት ማንም ሰው በቤቱ እንዲቀር አይፈቀድለትም። “የሎኮዋን” ድምፅ ሰምቶ በዱቡሻ አለመገኘት በወንጀል የሚያስጠረጥር ተግባር በመሆኑ ወደ ዱቡሻ ሳይመጣ የሚቀር ሰው የለም ።
በመሆኑም ዳውሮዎች ባህላቸው ለደነገገው ማህበራዊ ሕጎቻቸው ተገዢ በመሆናቸው ሠላም ወዳድና ለስርዓታቸውም ታማኝ ሕዝቦች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
በአጠቃላይ የዳውሮ ብሔረሰብ ባህላዊ የፍትህ ስርዓት “ዱቡሻ” ባህላዊ ህጎችና ደንቦች የሚከናወኑበትና በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለውና አከብሮት የሚሰጥ ባህላዊ ትውፊት ነው።
የባህላዊ ዳኝነትና ግጭት አፈታት ስርዓት በቀደምንት ስርዓቶች ትኩረት በመነፈጉ እየተዳከመ የመጣ ቢሆንም አሁን መንግስት ለዜጎች ባህላዊ ዕሴቶቻቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ታርካቸውንና ማንነታቸውን እንዲያሳድጉ በሰጠው ትኩረት እየተሻሻለ መጥቷል።
በመሆኑም የዳውሮ ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ዱቡሻ ሰፋ ያለና ጥልቅ ዕሳቤ ያለው በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ምርምር ቢያደርጉበት ለሀገርና ለዓለም ተሞክሮ የሚቀመርበት መሆኑን እ ለመግለጽ እንወዳለን።
በጌታሁን ግርማ
