

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ”ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ቃል 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና ምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በቦንጋ ከተማ አካኺዷል።
በመርሃ ግብሩ ወቅት ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች እንደገለጹት: ፓርቲው ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በወሰዳቸው እርምጃዎች ውስብስብ ችግሮችን መስመር እያስያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎቹ ተጠቃሚ ያልሆነ የሕብረተሰብ ክፍል ባይኖርም እንደ ደቡብ ምዕራብ ክልል ያለንን እምቅ አቅም በቱሪዝምና ግብርና ለዓለም ያስተዋወቅንበትና ወደ ስራ ዕድል የቀየርንበትን ምቹ መደላደል ፈጥረውልናል ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች።
ከዚህ ቀደም ከነበርንበት ድህነት ብልጽግና በሚመራው የለውጡ መንግስት እርምጃዎች የብርሃን ጮራ እያየን ስለሆነ ይኸንን ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ሊንወጣ አደራ የተቀበልንበት ዕለትም ጭምር ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በተለያዩ አስተዳደር ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ ከፋፋይ ሀሳቦችን ወደ አንድነት በማምጣት ገዥ ትርክትን ለማስረጽ አየሰራ ለጥላቻ ይውሉ የነበሩ ሀብትና ጉልበት ለልማት እያዋለ ተጨባጭ ለውጦች እያስመዘገበ እንዳለ አውስተዋል።
ፓርቲው አካታችነቱንና ሰው ተኮርነቱን በእያንዳንዱ ዜጋ ዘንድ እያስመሰከረ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች: የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተሳትፎ ከማረጋገጥ አንጻር የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና እውን ማድረጉ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በከተማና ገጠር አካባቢ ዜጎች ምቹና ጽዱ አካባቢ ላይ እንዲኖሩ ባስተዋወቀው የኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ ለበርካቶች የስራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ሀገራችንን በቱሪዝሙ ዘርፍ ተመራጭ እንዲትሆን እንዳስቻላት ገልጠዋል።
ሀገር ለማጽናት የሀሳብ የበላይነት ወሳኝ ነጥብ ነው ያሉት አባላቱ: ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በጽንሰ ሃሳብ የተወለደ እና ሃሳብን መሬት ላይ የሚተክል እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን እያሰፋ ያለ ፓርቲ ስለሆነ የኢትዮጵያን ልዕልና የሚፈልግ ዜጋ ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።
ብልጽግናን መምረጥና ማስመረጥ ድምጽ ከመስጠት ይልቃል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ: ሀገራችን በፓርቲው መሪነት የጀመረችው ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሳያዊና ኢኮኖሚያዊ ተደማጭነት ልቀው ወደ ታለመላት ከፍታ እንዲደርስ የሚያደርግ አደራም ጭምር ነው ብለዋል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
