በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 13ሺህ 365 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ፈተናን በበይነ መረብ እንደሚፈቱኑ የትምህርት ቢሮ አስታወቀ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ 184 ትምህርት ቤቶች 13 ሺህ 365 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተናቸውን በበይነ መረብ ለመፈተን ዝግጅት እየተጠናከረ መሆኑን ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመማር፣ ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር)ባቀረቡት ሰነድ ገልጸዋል።

በክልሉ የተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ ዘንድሮ 15 በመቶ ተወዳዳሪና ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን አጠቃላይ የትምህርት ይዘት በማጠናከሪያ ትምህርት መሸፈን፣ እንዲሁም ያለፉ ዓመታት የአስታንዳርድ ፈተናዎችን በመስራት ልምምድ ማድረግ በትኩረት እየተፈፀመ ነው ብለዋል ኃላፊዉ።

በተጨማሪም የተማሪዎች የስነ-ልቦና ግንባታን ማጠናከር፣ በራሳቸው እንዲተማመኑ ማድረግ እና ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲላመዱ የሚያግዙ ተግባራት አፅንዖት ተሰጥቷቸዋል።

ዘንድሮ በተለይ 2,286 ተማሪዎች በወረዳዎች መንግሥታትና በትምህርት ቤቶች በተደረገላቸው የምግብ ድጋፍ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በውሎ አዳር የፈተና ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውም ተገልጿል።

እንዲሁም የውሎ አዳር ትምህርት በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይም መጀመሩ በቀጣይ ሊጠናከር የሚገባ መሆኑ ተነስቷል።

የበይነ መረብ ፈተናውን በምቹ ሁኔታ ለማካሄድ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ተቋማት እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተዋቀረ ክልል አቀፍ ግብረ ሃይል መቋቋሙም ተገልጿል።

ግብረ ሃይሉ በኮምፒውተር፣ በብሮድባንድ ኢንተርኔት፣ በጀነሬተር አቅርቦትና በመሰል የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ላይ እየሰራ ሲሆን፣ ተቋማትን ለፈተና ተጋላጭ ተማሪዎች ክፍት በማድረግ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲላመዱ አበክሮ መሥራቱ ተጠቅሷል።

በመጨረሻም የዞን አመራሮች በሙሉ አቅም ተጠቅመው የትምህርት ስራውን መደገፍ እንዳለባቸው፣ መሰረተ ልማቶች ያልተሟሉባቸው አካባቢዎች ላይ የፈተና ማዕከላትን በመለየት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተነስቷል።

አሁን ላይ የትምህርት ቢሮ ሞክትል ኃላፊ ና የመማር፣ ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር)

በቀረበው ሰነድም ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

በበረከት ኢዮብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *