የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል ነው – ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

Spread the love

የኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የታሪክና የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት 130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ በሚገኘው መድረክ ላይ ነው።

የዓድዋ ድል ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ጎህ የፈነጠቀና ሰብዓዊ ክብርን ያጎናጸፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በዓለም አደባባይ ያስመሰከረና የሀገር ፍቅር ጽናትን ለዓለም የገለጠ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑንም አውስተዋል።

የዓድዋ አስተምህሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚያነግስ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ዓድዋ አጉራ ዘለል ፖለቲካንና ሌብነትን እንደሚጠየፍ አስረድተዋል።

የዘንድሮውን በዓል ስናከብር የድሉ እሳቤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ያለውን ከፍ ያለ ፋይዳ በማመላከት ጭምር መሆኑን አብራርተዋል።

አባቶቻችን የጥቁር ህዝቦችን ክብርና ነጻነት በመስዋዕትነት ማስከበራቸውን አስታውሰው፤ የዛሬው የዓድዋ ድል ትርጉም ነጻነትን በብልፅግና ማስዋብ፣ ለትውልዱ የሚተርፍ አኩሪ ተግባር መፈጸምና ማስተላለፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዓድዋን ስናስብ አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሉዓላዊነት የከፈሉትን ዋጋ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ሰፊ ርዕይ ጭምር መሆን አለበት ብለዋል።

በዓድዋ ድል ማግስት የዲፕሎማሲ ትግል አንዱ ማጠንጠኛ የነበረው ኢትዮጵያ ከዓለም የምትገናኝበትን የባህር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑንም አውስተዋል።

ኢትዮጵያውያን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ባደረጉት ተጋድሎ ታሪክ ለኢትዮጵያ መልካምና በጎ እንደነበር ያሳያል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።

ይሁን እንጂ በአልፎ ሂያጅ የፖለቲካ ስሌትና ኢትዮጵያዊነትን ባልዋጀ ሀሳብ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ መልህቃችንን እንዲሁም ጥቅሞቻችንን መስዋዕት አድርገን ቆይተናል ብለዋል።

የዓድዋ ድል ያስተማረን እንደ ባህር በር ባሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ከታሪክ ትክክለኛ ጎን መቆም መቻልን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ትላንት በዓድዋ አውድማ ላይ የተገኘው ወታደራዊ ድል ዛሬ በኢኮኖሚያዊና በጂኦ-ፖለቲካዊ ድል ሊደገም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብት የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የታሪክ አደራ የማይነጠል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሀገራችን የኢኮኖሚ ጥማት የሚረካውና የህዝቦቿ እጣ ፋንታ ብሩህ የሚሆነው ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ ወይም በየብስ እግረ-ሙቅ ያለመታሰሯን ስናረጋግጥ ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ዓድዋ ጀግኖች ሁሉ ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያን ጥቅም ማብሰር ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ መንገዳችንና መሻታችን ሰላማዊና በአብሮነት ማደግ ነው ብለዋል።

የባህር በር ጥያቄያችንን የታሪክና የፍትሕ ጥያቄ አድርጎ መረዳት እንዲሁም የትውልድ ህልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓድዋ ምን ጊዜም የግጭት ግለት ለሚሹና ሰላምን በመዝገበ ልቦናቸው ላልከተቱ ሁሉ ታላቅ መካነ እውቀት መሆኑን አስረድተዋል።

የዘመናችን ጀግንነትም የጭቅጭቅ ጩኸትን የሚያሰማ ሳይሆን፤ የሀገር ፍቅርን፣ እውቀትንና አብሮነትን የሚያጎላ መሆን አለበት ብለዋል።

ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማብሰር የዘመኑ የዓድዋ ድል መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ የትውልድ ህልውና መሆኑን መረዳት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊነትን ከእውቀትና ከአብሮነት ጋር አዋህዶ መጓዝ የትውልዱ አደራ መሆኑን በመግለጽ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *