


አገልግሎት አሰጣጥን ፍትሃዊና ቀልጣፋ በማድረግ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍና የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለሸካ ዞን አጠቃላይ አመራር፣ለወረዳና ከተማ አስተዳደር አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በቴፒ ከተማ ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።
ለአመራሩ ኦረንቴሽኑን የሰጡት የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊና የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙ በወቅቱ እንደተናገሩት በርካታ ተቋማት አካባቢ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውን አንስተው ይህንን ችግር ለመፍታትና የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የአመራሩ ድርሻ ጉልህ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አለማየሁ ምንም እንኳን ድሎች ቢኖሩም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በየደረጃው በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚስተዋልባቸው በክልሉ ምስለ ተገልጋይ በተረጋገጠው መሠረት የተቋማትን ዝርዝር ያቀረቡት አቶ አለማየሁ ከነዚህም መካከል ንግድና ኢንቨስትመንት ፣ገቢ፣ ግብርና፣ጤና፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ፣ፍትህና ፀጥታ ተቋማት (ፍትህ፣ፖሊስ)፣ ፋይናንስ፣በውሃ፣በትራንስፖርት ዘርፍ እና ሌሎችም ተቋማት ይገኙበታል ሲሉ አብራርተዋል።
የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ አመራሩና በየደረጃው የሚገኙ የየዘርፉ ባለሙያዎች ተግባራትን በጥብቅ ዲስፒሊን እንዲመሩ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን በአፅንኦት አንስተዋል አቶ አለማየሁ።
መልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ አገልግሎት አሰጣጣችንን በማዘመን እና ቀልጣፋ እንዲሁም ፍትሃዊ በማድረግ ህብረተሰቡን ለመካስ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኦረንቴሽን መድረኩ ላይ የተሳተፉ አመራሮች በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ተጨባጭ ለውጦች መኖራቸውን ጠቁመው ነገር ግን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል።
አመራሮቹ አክለውም የሚስተዋለውን ክፍተት በማረም የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ሲሉም አንስተዋል።
በቀጣይ ጊዜያት አገልግሎት አሰጣጡን ፍትሃዊና ቀልጣፋ በማድረግ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመቅረፍ የህዝቡን እርካታ በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ ላይ መግባባት በመድረስ መድረኩ ተጠናቋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
