የክልሉ ውሀ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀምና የቀሪ 3 ወራት የትኩረት አቅጣጫ ላይ የምክክር መድረክ በቦንጋ እያካሄደ ነው።

Spread the love

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ በዘርፉ የመጣው ለውጥ አመርቂ መሆኑን በማንሳት አሁንም ከግማሽ በላይ የሆነ የክልሉ ህብረተሰብ ክፍል የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ያለበት በመሆኑ በቁርጠኝነትና በቅንጅት መፍጠርና መፍጠንን በማከል መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የውሃ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በፍትሐዊ መንገድ ተደራሽ በማድረግ በየደረጃው ከህብረተሰቡን የሚነሱ ቅረታዎችን በመፍታት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይገባል ያሉት አቶ ነጋ ሀብትን በአግባቡ በማሰባሰብ የውሀ ተቋማትን በማስጠገንና በመንከባከብ አገልግሎትን በዘላቂነት መስጠት እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ብለዋል።

የማቺንግ ፈንድ በአግባቡና በጊዜ ገቢ ያለማድረግ የቀጣይ በክልሉ ውስጥ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ዕጣ ፋንታ ከመወሰንም በላይ በመንግስት ያልተገባ ወለድን በመጨመር እና ከመንግስት በጀት በመቆረጡ የሰብአዊ ክፍያ ሂደት ላይ ችግር እንደሚፈጥር በማንሳት ትኩረት እንደሚሻ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ህብረተሰባችን ከደህንነትና ተረጅነት ለማውጣት ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ እንዲሁም የአመራረት ዘይቤን በመቀየር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የመስኖ ዘርፍ ስራዎችን ማጠናከርና የባለድርሻ አካላት ልዩ ቅንጅትና ትኩረት እንደሚሻ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ አንስተዋል ።

የርዕሰ መስተዳድሩ መሠረተ ልማት አማካሪ ምትኩ በድሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው የውሃ ቦርድን በማጠናከር ወቅቱንና የህብረተሰብን አቅም ታሳቢ ያደረገ ክፍያ ስርዓት በመዘርጋት ተቋማዊ አሠራርን በመፍጠር የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ዘላቂ ማድረግና በተለያዩ መሠረተ ልማት ላይ በመናበብ የተቋማዊ ትስስር በማጠናከር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል ።

የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በማዕድን ማውጫ አካባቢ የመልሶ ማልማት ስራን በማጠናከር ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ ለማበርከት በቅንጅት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል ።

በውሃና መስኖ ዘርፍ የህዝብ ጥያቄን ለመመለስ ኢፍትሐዊ የተቋማት ስርጭትና ግንባታ በላይ የተገነቡትን በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ተመጣጣኝ የክፍያ ስርዓ መዘርጋት፣ የተቋማት አስተዳደር ስርዓት ማሻሻል እንዲሁም በዞንና ወረዳ አቅም ሊሰሩ የሚችሉ ተጨማሪ ተቋማትን የህብረተሰብ ተሳትፎን በማጎልበት በመገንባት የተሻለ ውጤት ለማምጣት በየደረጃው መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በማዕድን ዘርፍ የሚመራበት አግባብን መፈተሽ፣ ተጨማሪ አሰራርን መዘርጋትና ህገወጥነትን በጋራ በመቆጣጠርና በመከላከል በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል፣አልሚ ባለሀብቶች፣ የገባው የማምረቻ ማሽን እና ተመርቶ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማመጣጠን ከዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣የፕሮግራም ማቺንግ ፈንድ አፈጻጸም እና በክልል ደረጃ የከተሞች የውሃ አገልግሎት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይት ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላትና ከመድረኩ ምላሽ በመስጠት ሪፖርቱ ተጠቃሏል ።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *