



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ፥ ከጤና ሚኒስቴር እና አይካፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የቫይረስ መጠን ልኬት እና ተጋላጭ የጨቅላ ህጻናት ምርመራ የ2017 በጀት ዓመት ስምንት ወር አፈጻጸም ዙሪያ የተዘጋጀ የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ባለፉት 8 ወራት የፀረ-ኤች አይቪ ህክምና ላይ ያሉ ሰዎች የቫይረስ መጠን ልኬት ሽፋን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ ባለፋት የክልሉ ምሥረታ ወቅት አፈጻጸሙ ከነበረበት አጅግ ዝቅተኛ ሽፋን አሁን 69 ከመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ የተጋላጭ ጨቅላ ህጻናት ምርመራ አሁንም በክልሉ ዝቀተኛ መሆኑን በማመላከት መድረኩ በአፈጻጸሙ ወቅት በገጠሙ ችግሮችና የመፍትሔ አማራጭ በጥልቀት ውይይት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በክልሉ አጠቃላይ የዘርፈ ብዙ ኤችአይቪ ኤድስ፥ የቫይረስ መጠን ልኬት እና ተጋላጭ የጨቅላ ህጻናት ምርመራ አፈጻጸም ወጥ በማድረግ አፈጻጸም ማሳደግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ሀይሌ ተግባሩ እንዲሳካ የባለድርሻ አካላት እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ ኤድስ ድጋፍና እንክብካቤ ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ምህረት ጌታቸው በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የቫይረስ መጠን ልኬት እና ተጋላጭ የጨቅላ ህጻናት ምርመራ አፈጻጸም ዝቀተኛ ከኾኑባቸው ክልሎች አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መሆኑን በመጥቀስ በክልሉ ባለፋት 4 ወራት በዘመቻ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በቀሪ ሁለት ወራት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የቫይረስ መጠን ልኬት እንዲያደርጉ ግንዛቤ መፈጠርና ሁኔታዎችን በማመቻቸት አፈጻጸሙ አሁን ከደረሰበት በተሻለ መልኩ ማሳደግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ኃላፊዋ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካሉ ቤተሰብ ለሚወለዱ ልጆች በተቀመጠው መመዘኛ መሠረት ተገቢውን ምርመራና የህክምና ድጋፍ በማድረግ ስርጭቱን መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።
የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ውጤታማነት ለማረጋገጥ የቫይረስ መጠን ልኬት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ምህረት የመድረኩ ተሳታፊዎችጰበክልሉ ለተግባሩ አፈጻጸም ማነቆ የኾኑ ጉዳዮችን በመለየት መፍተሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ የ2017 በጀት ዓመት የ8 ወራት የቫይረስ መጠን ልኬት እና ተጋላጭ የጨቅላ ህጻናት ምርመራ አፈጻጸም ቀርቦ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን፥ በመድረኩ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የክልልና የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ተወካዮች
እንዲሁም የአጋር ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
