



የሸካ ዞን ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረኃይል የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በተመለከተ በሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቴፒ ከተማ አካሂዷል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የግብረኃይሉ ሰብሳቢ አቶ አበበ ማሞ በውይይት መድረኩ እንደገለፁት በዞኑ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ብሎም በአጠቃላይ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር እና ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ከአካባቢያችን በኮንትሮባንድ የሚወጡ ምርቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥርን ማጠናከር ፣በተገቢው መምራትና የእርምት እርምጃ መውሰድ ላይ ግብረኃይሉ በተጠናከረ መንገድ መስራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
በተለይ በዞናችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ ያለውን የቤንዚን የዋጋ ንረትና ህገ ወጥነትን ለመከላከል በዞኑ ፈቃድ የተሰጣቸው ማደያዎችና የነዳጅ ቸርቻሪ ማህበራት ህግና ስርዓትን ተከትለው እያሰራጩ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በዞኑ ፈቃድ ሳይኖራቸው በነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት ህገ ወጥ በመሆናቸው አስፈላጊውን ክትትል ማድረግና ተገቢውን እርምጃም መውሰድ እንደሚገባ አቶ አበበ አሳስበዋል።
የሸካ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሠለ አበበ በበኩላቸው በአጠቃላይ ከነዳጅ ግብይት አንፃር ብልሽት መኖሩን ጠቁመው በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮችና አመራሮች የነዳጅ ግብይቱ ተገቢ በሆነ በንግድ አሰራር ስርዓት እንዲመራ መስራት እንዲሁም በመቀናጀትና በመናበብ አሠራር ስርዓቱን ጠብቆ መምራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በየመዋቅሩ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት ለመከላከል የህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረኃይል በተቀናጀ መንገድ መምራት አለበት ብለዋል።
የሸካ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ፀዳሉ ነችቶ በህገወጥ መንገድ ስዘዋወርና ሲሸጥ የነበረ ናፍጣ 7ሺህ 5መቶ ሊትር እና ቤንዚን 5ሺህ 4መቶ 29 ሊትር በድምሩ 12ሺህ 9መቶ 29 ሊትር መያዙን ገልፀው ተሽጦ ለመንግስት ገቢ መደረጉን አንስተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ውስጥ ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በተገቢው በመፈተሽ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በቀጣይም በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ማደያዎች በህገ-ወጥ መንገድ ግብይት ሲፈጽሙ ከተገኙ ማደያውን በማሸግ የንግድ ፈቃዱን በመሠረዝ በህግ የማስጠየቅ ስራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል አቶ ፀዳሉ፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎችም አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ግብረኃይሉ ህጋዊ አሰራርን በመከተል የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ህዝብ ላይ ያለውን ከፍተኛ ጫና ማስቀረት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በህገ ወጥ ንግድና ቁጥጥር ላይ ከነዳጅ፣ መድኃኒትና ቡና ግብይት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የህግ አሰራርን መተግበር ይገባል ሲሉም በአፅንኦት አንስተዋል።
ማደያዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፈተሽና የቁጥጥር ስራን በማጠናከር ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል።
የነዳጅ ግብይት በተለይ ከቤንዚን እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር አሰራር ስርዓትን ተከትሎ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ውይይቱ ተጠናቋል ሲል የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
