መልካም አስተዳደር ለማስፈን በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የክልልና የዞን ምክር ቤቶች 5ተኛ ዙር የጋራ ምክክር ፎረሙ በሁለተኛ ቀን ውሎ የተመረጡ የዞን ምክር ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለፎረሙ አባላት ቀርቦ ተወያይተውበታል።

በዚህ ወቅት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ ምክር ቤቶች በየ ደረጃው የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ማነቆችን በዘላቂነት በመፍታት በሁሉም ዘርፍ የማኅበረሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮችን በማመቻቸት አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት በመረዳት የህዝብ ዉክልናን በተገቢው ሊወጡ ይገባልም ስሉ ገልጸዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሐይ ዳርጫ በበኩላቸው በሁሉም ዘርፍ የታዩ መልካም ጅምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በማህበራዊ ዘርፍ ላይ ከትምህርት፣ ከጤና ጋር ተያይዞ የግብኣት አቅርቦት እጥረትና ማዐጤመ ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ መሥራትን ይጠይቃልም ተብሏል።

በምክር ቤቶች ተሳትፎ የተሠሩ ተግባራት ተስፋ ሰጪ እንደሆኑም ተጠቁሟል።

ምክር ቤቶች በግብርናው ዘርፍ የማኅበረሰብን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ ያሳሰቡት የክልሉ ምክር ቤት ግብርናና ገጠር ልማት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዲስ ምዕራፍ ዓለሙ ናቸው።

የዳውሮ፣ የካፋና የቤንች ሽኮ ዞኖች የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤዎች ቀርቧል።

በበጀት ዓመቱ በምክር ቤቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ጥሩ መነሻ ተደርገው ተወስደዋል።

በዕቅዱ መነሻ ለአፈፃፀም ማነቆ የሆኑ እና መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ዙርያ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የዞን ምክር ቤቶች የ6 ወራት አፈፃፀም ድጋፍዊ ክትትል ግብረ መልስ ከክልሉ ምክር ቤት ለምክክር ፎረሙ አባላት ቀርቧል።

ከፎረሙ አባላት ለተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ የምክክር ፎረሙ ተጠናቅቋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *