ቢሮው በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ይገኛል።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን በመክፈት የህብረተሰቡን የመድኃኒት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ እንደሚገኝ የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ገልፀዋል።

አቶ ኢብራሂም ተማም በታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል በኢት ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር፣ በክልሉ ጤና ቢሮ፣ በዳውሮ ዞን አስተዳደር ፅ/ቤት፣ በታርጫ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤትና በታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ የተሰራውን የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት አስመርቀዋል።

ሀላፊው የተመረቀው የታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት በአከባቢው የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የማይተካ ሚና እንዳለውም አብራርተዋል።

ለመድሀኒት ቤቱ ግንባታና መደራጀት የተባቡሩትን ሁሉ ያመሠገኑ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ የሆስፒታል ቡርዱ ለመድሀኒት ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ ሌንጫ የመድኃኒት ቤት መከፈቱ የሆስፒታሉን የአገለግሎት አሰጣጥ ተደራሺነት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

የታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል ማህበረሰብ መድኃኒት ቤት የከተማውን ማህበረሰብ የጤና ተጠቃሚነትን እንደሚጨምር የገለፁ የታርጫ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ ናቸው።

ለመድሀኒት ቤቱ ግንባታ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገ የገለፁ የኢት ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ወንድሙ ምትኩ አክሲዮን ማህበሩ በጤናና በትምህርት ዘርፍ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በቦታው የተገኙ የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች በመድሀኒት ቤቱ መከፈት መደሰታቸውን ገልፀው መድኃኒት ቤት እንዲከፈት የተባበሩትን አመሰግነዋል ሲል ደሬቴድ ዋካ ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *