የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብልፅግና ተግቶ እየሠራ መሆኑ ተጠቆመ

Spread the love

በብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ከተማ አቀፍ የህዝብ መድረክ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩን እየመሩ የሚገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል እንደተናገሩት ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በከተሞች ደረጃ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ እየሠራ መቆየቱን ገልፀው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከተሞችን ማልማትና ለነዋሪዎች ምቹና ሳቢ ማድረግ እንዲሁም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ውስጥ ዋነኛው በመሆኑ ይህንኑ ማረጋገጥ መፈፀምና ማስፈፀም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ሲሉም ጠቁመዋል ኢንጂነር የማታለም።

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በወቅቱ እንደገለፁት ብልፅግና ፓርቲ በመደበኛ ጉባኤው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችን በመፈፀምና በማስፈጸም የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸው ድሎች ቀላል የማይባል መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበበ ማሞ በቀጣይ በልዩ ትኩረትና ፍጥነት ትኩረት ልሠሩና ልፈቱ የሚገቡ ጉዳዮችን በጉባኤው በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ይሠራል ሲሉም አንስተዋል።

በመድረኩ በቴፒ ከተማ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን እና በቀጣይ በሚሠሩ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ የተዘጋጀውን ሠነድ የከተማው ከንቲባ አቶ ወንድሙ ግርማ እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ሠነዶችም ቀርበው ውይይት ይደረግበታልም ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *