



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን በዘንድሮ 2017/18 መኸር እርሻ 3ሺህ 122 ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት እየለማ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና፣አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ አስታውቀዋል ።
የዞኑ ግብርና፣አከባቢ ጥበቃና የህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳለኝ ፤በዞኑ በመኸር ወቅቶች በሩዝ ምርት እርሻ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማሳ ሽፋን፣የምርታማነት ዕድገትና የአርሶ አደሮች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በባለፈው ዓመት መኸር እርሻ 1,950 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ ምርት መልማቱን ያስታወሱት ኃላፊው ዘንድሮ የማሳ ሽፋንም ሆነ ምርታማነት ለማሳደግ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገው ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እና የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር የጋራ ምክክር መድረኮችን በማካሄድና ለግብርና ባለሙያዎች ከዘር ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ ፓኬጅ ላይ ሥልጠና መሰጠቱንም አክለዋል።
በዞኑ በዘንድሮ 2017/18 መኸር እርሻ 3ሺህ 122 ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት እየለማ እንደሚገኝም የገለጹት አቶ አዕምሮ ደሳለኝ ከዚህም 123 ሺህ 4 መቶ ኩንታል ምርት ይጠበቃልም ብለዋል።
በመኸር ወቅቱ ከሚለማው ማሳ የሚጠበቀዉን ምርት ማግኘት እንዲቻል የግብርና ባለሙያዎች ምክር ሀሳብ፣የፀረ-ተባይና አረም ቁጥጥር እንዲሁም በየደረጃው የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክሮ እየተሰሩ ይገኛሉም ብለዋል ኃላፊዉ።
በዞኑ በሩዝ ምርት እርሻ ሥራ የማሳ ሽፋንም ሆነ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም አንዳንድ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂን የመጠቀም ዝንባሌ አነስተኛ በመሆኑ በምርትና ምርታማነት ላይ ማነቆ እያሳደረ ስለሚገኝ ቀጣይ ችግሩን ለማረም በልዩ ትኩረት ሥራዎች ይተገበራሉ ነዉ ያሉት።
በፍቅር ከበደ
