




በዳውሮ ዞን የሎማ ቦሳ ወረዳ እና የገሳ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የብልጽግና ፓርቲን ዓላማና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ማካሄድ ጀምረዋል።
ዛሬ ረፋዱን በገሳ ከተማ በተጀመረው በዚህ ሰልፍ ላይ የየአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች በነቂስ ወጥተው ድጋፋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ሰልፈኞቹ የፓርቲውን ዓላማ የሚደግፉና የመንግሥትን የለውጥ ጉዞ የሚያበረታቱ ልዩ ልዩ መፈክሮችን እያስተጋቡ ነው።
በሰልፉ ”ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ስኬት በቁርጠኝነት እንቆማለን!” ፤”በአካባቢያችን እየተመዘገቡ ያሉ የልማትና የመሠረተ ልማት ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ! ፤”ሰላማችንን በመጠበቅ ለሀገራዊ አንድነታችን ዘብ እንቆማለን!” በማለት ድምፃቸውን አሰምተዋል።
የሰልፉ አስተባባሪዎች እንደገለጹት፤ ይህ የድጋፍ ሰልፍ ሕዝቡ በመንግሥት እየተከናወኑ ባሉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ያለውን አመኔታ የሚያሳይ ነው። በተለይም በአካባቢው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፍላጎታቸውን እየገለጹ መሆኑ ታውቋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የዞንና የሎማ ቦሳ ምርጫ ክልል ዕጩዎች፣ የክልል፣ ዞን፣ወረዳው እና ገሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለአካባቢው ነዋሪዎች መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተሳታፊዎቹም ለልማትና ለሰላም መጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ቃል እየገቡ ሰልፉ በሰላማዊ ሁኔታ ቀጥሏል ሲል የዘገበው የዋካ ኤፍ ኤም ነው።
