7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፣ ሁሉም ፓርቲዎች ለምርጫው ስኬት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ተጠየቀ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውይይት በቦንጋ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጋራ ምክር ቤቱ የውይይት መድረክ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፤ በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ላይ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

መጪው ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና የሀገረ መንግስት ግንባታው የሚፀናበት የታሪክ ምዕራፍ እንዲሆን፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው አቶ ፍቅሬ ያሳሰቡት።

የጋራ ምክር ቤቱ በቅድመ ምርጫው ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን በውይይት እየፈታ መምጣቱን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ፓርቲዎች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫን ለማካሄድ የሚደረገው ጥረት ስኬታማ የሚሆነው ሁሉም ወገኖች የፉክክርና የትብብር ሚዛንን በጠበቀ መልኩ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ሲችሉ መሆኑን ጠቁመው፤

ከዚህ በተቃራኒ የሀገርን ሰላም የማይሹ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶችን ሴራ በጋራ መመከት ወቅቱ የሚጠይቀው የማይታጠፍ አቋም መሆኑን በአፅንኦት አሳስበዋል።

በሀገራችን የተከማቹ ፖለቲካዊ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት የተጀመረውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ በሙሉ አቅም መደገፍ ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፣

እስካሁን በቅድመ ምርጫ ሂደቱ የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር የክልሉን ልማትና መልካም አስተዳደር በትብብር ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ባሻ በመድረኩ የመወያያ ሰነድ እያቀረቡ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *