በሸካ ዞን ግብርናን ለማዘመን የሚያስችሉ የ117 ሚሊዮን ብር የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ከ117 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

በክልሉ የግብርና ቢሮ በምግብ ስርዓተ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ የሚገነቡትን የእነዚህን ፕሮጀክቶች መሠረተ ድንጋይ ያስቀመጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው።

በዞኑ ያለውን እምቅ የግብርና አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የተጀመሩ እነዚህ ፕሮጀክቶች፣ በተለይም የገንጂ አነስተኛ መስኖና የጌጫ ከተማ ሁለገብ መጋዘን ግንባታን ያካተቱ ናቸው።

የመስኖ አውታር መዘርጋቱ የክልሉን የግብርና ሥራ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ አርሶ አደሩ በዓመት ውስጥ ደጋግሞ እንዲያመርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ይህ ግብርናን የማዘመን እንቅስቃሴ አርሶ አደሩ ራሱን በምግብ ከመቻል ባለፈ፣ ትርፍ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን በዘላቂነት እንዲያረጋግጥ ያስችለዋልም ብለዋል።

አቶ ማስረሻ በላቸው እንደገለጹት፣ መንግሥት በአካባቢው የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት የክልሉን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ሁሴን በበኩላቸው፣ ግንባታዎቹ በተቀመጠላቸው ጥራት ተጠናቅቀው ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በአከባቢው ፍትሀዊ የልማት ተደራሽነት ችግር በመኖሩ በህብረተሰቡ ዘንድ የሰነበተ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መኖራቸውን የገለጹት የዞኑ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አለማየሁ አለሙ፣ አሁን ግን በለውጡ መንግሥት የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መኾኑ ግልጸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *