ቢሮው የአሰሪና ሠራተኛ ዘርፍ የአማካሪ ቦርድ ምሥረታ አካሄደ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሥራ ክህሎት ቢሮ፤ የአሰሪና ሠራተኛ ዘርፍ የአማካሪ ቦርድ ምሥረታ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።

ከአሰሪ፣ ከሠራተኛ እና ከመንግሥት ወገን የተወጣጡ 15 አባላት ያሉት የአማካሪ ቦርድ ተሰይመው በጉባኤው ፊት ቃሌ-መሀል ፈጽመዋል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቢሮው ምክትልና የአሰሪና ሠራተኛ ዘርፍ ኃላፊ ተክሌአብ ቡሎ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ የአማካሪ ቦርድ መመሥረት በአሰሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች በመፍታት ሠራተኞች ዕድሎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታን የሚፈጠር መሆኑን ተናግረዋል።

አማካሪ ቦርዱ በየደረጃው የሚወጡ የአሰሪና ሠራተኛ ደንቦችና ህግጋትን ለማስፈጸም የጎላ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ተክሌአብ ቦርዱ በአሰራና ሠራተኛ መካከል መተማመን እንዲፈጠር በማድረግ፤ የሠራተኞች ጥቅም በተገቢው ተከብሮ አሰሪዎች ምርታማነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።

በስራ ላይ ደንነትና ጤንነት እንዲሁም በውጭ ሀገራት የሥራ-ስምሪት ላይ አማካሪ ቦርዱ የማማከር ሚናውን በመወጣት አስገዳጅ ህጎችን የማስፈጸም ተግባር እንደሚወጣ ያስገነዘቡት ዶ/ር ተክሌአብ የቦርዱ አባላት ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተወጣጣ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ለክልሉ ከተሰጠው የውጭ ሀገራት የሥራ-ስምሪት ኮታ ውስጥ 3ሺህ 710 ዜጎችን ብቻ በማሰልጠን ወደ ወጪ ሀገራት መላክ መቻሉን የገለጹት ዶ/ር ተክሌአብ ይህም አሀዝ ከተሰጠው 42ሺህ የክልሉ ኮታ አኳያ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ የሚቋቋመው የአማካሪ ቦርድ በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚሰራበት አንዱ ዘርፍ መሆኑን አንስተዋል።

በአማካሪ ቦርዱ ዓላማና አስፈላጊነት እንዲሁም ዝርዝር ተግባራት ላይ በስራና-ክህሎት ሚኒሰቴር የተዘጋጀውን ሰነድ በቢሮው የሠላማዊ ኢንዱስትሪ ግኑኝነት ዳይሬክተር ወ/ሮ አበዛሽ ወ/ጊዮርጊስ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን፣ በሚዛን አማን እና በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተሞች ተቋቁሞ ወደ ተግባር የገባው የወሳኝ ቦርድ ተግባር ላይ የመስክ ምልከታ ሪፖርትና ግብረ-መልስ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል።

በመድረኩ የአማካሪ ቦርድ አባላት፣ የወሳኝ ቦርድ ሰብሳቢዎች፣ የዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊዎችና እና ሌሎች ተግባሩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *