በዳውሮ ዞን ጌና ወረዳ የኬሚካል ርጭት በማድረግ የወባን ጫና ለመቆጣጠር በከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነዉ

Spread the love

በጌና ወረዳ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሁሉም ቀበሌዎች ቤት ለቤት የወባ ኬሚካል ርጭት ዘመቻ በስፋት እየተካሄደ ነው። የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፣ ይህ እርምጃ ከክልሉ መንግስት በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ጌና ወረዳ 100% የኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

የወረዳው ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘነበ ዳማኮ ከኬሚካል ርጭቱ በተጨማሪ ሌሎች የተቀናጁ የመከላከያ መንገዶችም በስራ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ኃላፊው በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው “ወባ ከቁጥጥር ውጭ ነው” የሚለውን መረጃ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ዘነበ ዳማኮ: “የዛሬ ሁለት ዓመት የተነሳን ፎቶ በመውሰድ የወባ ጫና ከተቋማችን አቅም በላይ ነው ብሎ ማሰራጨት ተገቢ እንዳይደለና የወባ ጫና ከአቅም በላይ ነው የሚባለው በህጋዊ አካላት ሲረጋገጥ ብቻ ነው በማለት ገልፀዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በወረዳው ያለው የወባ ጫና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግልጽ መሻሻል ታይቷል።”ብለዋል።

አቶ ዘነበ አሁን ባለው ርብርብ፣ በቋሚና ጊዜያዊ የወባ መራቢያ ቦታዎች ላይ ጭምር ‘አኳታብ’ የተባለ ኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የወልደ ሃኔ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ምትኩ ገቲሣ በበኩላቸው፣ የጤና ተቋሙ ለህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

አቶ ምትኩ የክረምት ወራት መውጣትን ተከትሎ የሚጨምረውን የወባ ጫና ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፤ በማኅበራዊ ሚዲያ የወጡ መረጃዎች ግን ከተቋሙ አለመወሰዳቸውንና ትክክለኛ መረጃ አለመሆኑን አረጋግጠዋል።

ኃላፊዎቹ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭቱ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ እንዲሆን፣ ባለሙያዎች ቤት ለቤት በሚዘዋወሩበት ወቅት ህብረተሰቡ የቤት ውስጥ ርጭት እንዲካሄድ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ሲል የጌና ወረዳ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *