

መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በጀመራቸው እርምጃዎች የዋጋ ንረትን በአንድ ዓመት ውስጥ ከ30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 36ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
በዚህም የኑሮ ውድነት የዓለም ዋነኛ አጀንዳና አገራትን እየፈተነ ያለ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት፤ ኢትዮጵያም የዚህ ፈተና ሰለባ መሆኗን ተናግረዋል።
መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ልማትን ከማፋጠንና የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ጎን ለጎን ለምርታማነት ማደግ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል።
በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ወሳኙ መፍትሔ በመሆኑ ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ ሥራ ሰርተናል ነው ያለት።
በኩታ ገጠም፣ በሩዝ፣ በስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በምገባ ማዕከላት፣ ሰፋፊ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።
በዚህም ዓመት በሰብል ምርት ከአምናው 100 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ መሰብሰቡን ገልጸው በሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር በዶሮና በእንቁላል ምርት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ዋጋ ማርገብ ተችሏል ብለዋል።
መንግሥት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለነዳጅና ለማዳበሪያ ከፍተኛ ድጎማ ማድረጉን ጠቅሰው ምግብ ነክ የሆኑ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር እፎይታ ማድረጉን ተናግረዋል።
በዚህም መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች የዋጋ ንረቱን አምና ከነበረበት 30 በመቶ ዘንድሮ ወደ 23 በመቶ ዝቅ ማድርጉን ጠቅሰዋል።
መንግሥት አሁንም የዋጋ ንረት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ በተቀናጀ ርብርብ ጫናውን ለማቃለል እየሰራ ነው ብለዋል።
