

በግብርና የዚህ ዓመት ዕቅዳችን 7 ነጥብ 3 እድገት እናረጋግጣለን፤ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት እናመርታለን የሚል ነው።
ባለፉት 6 ወራት በተለይ ክረምት ላይ ከፍተኛ ምርት የተገኘበት ዓመት ስለሆነ 6 ወር በሰራነው ሥራ 999 ሚሊየን ኩንታል መሰብሰብ ተችሏል። ይህም ከዓመቱ ዕቅድ 78 በመቶ የሚሸፍን ነው።
በሰብል፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በጥጥ ምርት የዓመቱን ዕቅድ 79 በመቶ በ6 ወር መሸፈን ተችሏል፤ በሚቀጥሉት 6 ወራትም ይህንን አጠናክረን ከቀጠልን ካሰብነው በላይ ማሳካት እንችላለን።
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር 88 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ከ19 ሺህ በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች በማሰማራት የቤት ለቤት መረጃ የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ ሲሆን÷ ይህ ሲጠናቀቅ በርካታ አዳዲስ መረጃዎች እንደምናገኝ ይጠበቃል።
ከዚህ የመረጃ መሰብሰብ ስራ የግብርና ዘርፍን ብንመለከት በኢትዮጵያ፡-
• ትራክተር በ2010 ዓ.ም 4 ሺህ 700 ገደማ እንደነበር እና አሁን ላይ ወደ 27 ሺህ 200 አድጓል።
• ኮምባይነር በ2010 ዓ.ም 338 ገደማ የነበረ ሲሆን÷ ዛሬ ላይ 8 ሺህ 700 ኮምባይነር አለ።
• የግለሰብ የውሃ ፓምፕ በ2010 ዓ.ም 6 ሺህ ገደማ የነበረው ወደ 280 ሺህ ከፍ ብሏል።
አጠቃላይ ውጤቱ ሲደርስ የሚገለጽ ቢሆንም በመረጃ አሰባሰቡ በተገኘው መረጃ መሰረት በግለሰብ አርሶ አደሮች ደረጃ በክላስተር እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የመጣው እድገት ከፍተኛ ነው።
የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከግብርና ተረፈ ምርቶች ኮምፖስት የማዘጋጀት ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሰራው ስራ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ፣ በሚሊየን ሄክታር የሚጠጉ መሬቶች ወደ እርሻ በመጨመሩ፣ የበጋ እርሻ፣ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች የግብርና ሂደትን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽለዋል።
አሁን ላይ ደግሞ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ መስራት ብቻ በቂ አይደለም ብለን በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪዎች የማዘጋጀት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ይህም እንደ የአካባቢው ምርት እና የመሬት ዓይነት ተስማሚ የሆነ የአፈር ማዳበሪያ ማቅረብ የሚያስችል ጥናቶች እየተጠናቀቀ የሚገኝ ሲሆን÷ በዚህም አሁን ካለው ምርት በእጅጉ እንዲያድግ ያደርጋል።
አሁንም በመጣው በየትኛውም ዘመን ታይቶ የማያውቅ አመርቂ ውጤት ሳንኩራራ ከዚህ በላይ በመስራት ምርታማነት እንዲያድግ መስራት ያስፈልጋል።
