



በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የልማት ክፍተት ለመሙላት መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን በካፋ ዞን፣የኦዲዮ ካካ ምርጫ ክልል የኢፈዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና የክልል ምክር ቤት ተመራጮች ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በአዲዮ ካካ ወረዳ እየተገነባ ያለውን የውሃ መሠረተ ልማት ስራዎች ተዘዋውሮ የጎበኙ ሲሆን በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር በመቀናጀት ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረጉት ያለው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል።
በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የምክር ቤቱ አባል የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ኢንጂነር በየነ በላቸው የካካ ከተማ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሁለት ተቋራጮች ተከፍሎ በክልሉ መንግሥት የበጀት ድጋፍ እየተገነባ መሆኑን በመግለጽ በዚህም የአንድ ጥልቅ ጉድጓድ ስራው ተጠናቀው ውሃውን ከጥልቅ ጉድጓድ ለማውጣት የሚያስችል አስፈላጊ የኤሌክትሮ-መካኒካል ግብዓቶች መቅረባቸውን አመላክተዋል።
ከዚህም ባሻገር ውሃን ከምንጩ ወደ ዋናው ማጠራቀሚያ የሚያደርስ የመስመር ዝርጋታ መከናወኑን የገለጹት ኃላፊው ይሁን እንጂ የማጠራቀሚያ ግንባታ በተያዘው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ መዘግየት ተስተውሏል ብሏል። ይህንንም ችግር ለመፍታት ከተቋራጩ ጋር በመነጋገር የማጠራቀሚያ ግንባታ፣ ወደ ከተማ ውሃ የሚያደርስ የማከፋፋያ የመስመር ዝርጋታ እና የቦኖ ግንባታ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጦ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የ500 መቶ ሺህ ሊትር ውሃ የሚይዝ ማጠራቀሚያ ግንባታው የጣሪያ ሽፋን ስራ መጀመሩን የገለጹት ኢንጂነር በየነ፥ 2.4 ኪሎሜትር የከተማ ውስጥ ለውስጥ መስመር ዝርጋታ መከናወኑንና ቀሪ የ2.3 ኪሎሜትር የውስጥ ለውስጥ የተጠቃሚ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የቦኖ ግንባታን በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ቢሯቸው በልዩ ትኩረት ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የወረዳው የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መቅደስ አለሙ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የካካ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት አድንቀው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማው የውሃ ችግር ይቀርፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለ15 ሺህ የካካ ከተማና አጎራባች ቀበሌዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ የማቅረብ አቅም እንዳለው ያነሱት ኃላፊዋ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአግልግሎት እንደበቃ ህብረተሰቡ በሀሳብና በጉልበት እየደገፈ መሆኑን በመግለጽ የህዝብ ተመራጮች የህዝባቸውን የልማት ምላሽ አፈጻጸም ለመከታተል በመምጣታቸው አመስግነዋል።
በኢፈዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ክብርት ወ/ሮ ፋናዬ መለሰ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን በማንሳት ሌሎች ምላሽ ያላገኙ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችም በተገቢው መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ጉብኝት ላይ የተገኙት የአዲዮ ካካ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገረመው ገብሬ ፕሮጀክቱ ተጠናቀው ለአግልግሎት እንዲበቃ የወረዳው መንግሥት ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደማይለው ገልጸዋል።
አስተዳዳሪው አክለው የክልሉ መንግሥት በከተማውን የሚታየውን የውሃ ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
