





በ2015 ዓመተ-ምህረት በጊንቦ ወረዳ አስተዳደር የበጀት ድጋፍና በማህበረሰቡ ተሳትፎ የተጀመረው ባለ 2 ወለል እና 12 መማሪያ ክፍሎች ያሉት የህንፃ ግንባታ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትመህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፣ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሜ፣ የካፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አጥናፉ ሃይሌ እና የወረዳው ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎችና የዞንና የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የጊምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1943 ዓመተ-ምህረት በሳር ቤት የጀመረውን የመማር ማስተማር ሥራ በ1952 ዓመተ-ምህረት ደግሞ መደበኛ የትምህርት ቤት እውቅና በማግኘት ወደሥራ ገብቷል፡፡
የህንፃ ግንባታው 24 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን በቀጣይ ትምህርት ቤቱን አዳሪ ትምህርት ቤት ለማድረግ ዕቅድ መኖሩም ተገልጿል፡፡
የትምህርት ቤቱን የቀድሞ ተማሪዎች በማስተባበር የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት መማሪያ ክፍሎችን ስማርት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ የወረዳው ቀበሌዎች የሚመጡ በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረም ቆይቷል፡፡
የትምህርት ቤቱ ደረጃውን ጠብቆ መገንባት የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር ጉልህ ሚና የጫወታል ተብሎ ይጠበቃል ደሬቴድ ቦንጋ ቅርንጫፍ ዘግቧል።
