




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኮንታ ዞን አመያ ከተማ የብልፅግና ፓርቲን የሚደግፍና ህዝባዊ መሰረቱን የሚያሳይ ታላቅና ደማቅ ሰልፍ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የአመያ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ከጠዋቱ ጀምሮ አደባባዮችን በፓርቲው አርማዎች፣ ባነሮችና በተለያዩ መፈክሮች በማጌጥ፣ ለብልፅግና ፓርቲ ያላቸውን የማይናወጥ ድጋፍና አጋርነት በታላቅ የደስታ ስሜት እየገለጹ ይገኛል።
ህዝባዊ ሰልፋ የብልፅግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱና በክልሉ፣ በተለይም በኮንታ ዞን ላስመዘገባቸው ሁለንተናዊ የልማትና የፖለቲካ ስኬቶች እውቅና የሚሰጥና በቀጣዩ ምርጫም ለፓርቲው ይሁንታ የሚሰጥ ነው።
ሰልፈኞቹ በሰላም ግንባታ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በኢኮኖሚ የተመዘገቡት የለውጥ ውጤቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ መሆናቸውን እየገለጹም ይገኛል።
“የጀመርነው የለውጥና የብልፅግና ጉዞ በፓርቲያችን መሪነት ይቀጥላል!” የሚሉት መፈክሮችም የፓርቲው የፖሊሲና የስትራቴጂ አቅጣጫዎች በህዝቡ ዘንድ ምን ያህል ጥልቅ ተቀባይነትና እምነት እንዳላቸው በተግባር ያሳዩ ሆነዋል።
የኮንታ ዞን ነዋሪዎች በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ድምጽ የሚሰማ፣ የህዝብን ችግር የሚፈታና በተግባር የሚያሳይ እውነተኛ የህዝብ ፓርቲ መሆኑን መስክረዋል።
ባለፉት ዓመታት በዞኑ የታዩት ተጨባጭና የሚታዩ የልማት ለውጦች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ህዝቡ ከፓርቲው ጎን በፅናት እንደሚቆምም ሰልፈኞቹ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም በመጪው 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጻቸውን ለብልፅግና ፓርቲ በመስጠት፣ የተጀመረውን የለውጥ እና የሪፎርም ጉዞ ወደ ላቀ የስኬት ማማ ለማሸጋገር ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መኾናቸውን እየገለጹ ይገኛል።
በዚህ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ በደመቀው የድጋፍና የምርጫ ቅስቀሳ ሰልፍ የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ ሌሎች በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
