የቢስት ባር የመደመር አስተሳሰብ በተግባር የሚገለጽበት በዓል ነው ።ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ።

Spread the love

የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

በዚሁ ሁነት የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ጸጋን የታደለ ድንቅና የራሱ ታሪካዊ ዳራ ያለበት ህዝብ የሚኖርበት ነው ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የቤንች ብሔር የራሱ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ እሴቶች ደግሞ የቢስት ባር “የዘመን መለወጫ”በዓል ሲሆን ከሩቅም ከቅርብም ያሉ በጋራ ተሰባስበው የሚያከብሩት ለህጻናትና ለወጣቶች ምክር የሚሰጥበት የመደመር አስተሳሰብ በተግባር የሚገለጽበት በዓል ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

ይህ የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ ቢስት ባር ታሪካዊ ዳራው በተገቢው ተጠንቶ ለትውልዱ ሊተላፍ ይገባልም ብለዋል።

የብሔረሰቡ ምሁራን ለአካባቢው ልማትና ዘላቂ ሰላም ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የቤንች ብሔርና የአካባቢው ነዋሪዎች በትላልቅ ፕሮጀክቶች ተፈጻሚነት ላይ ያሳዩት ተሳትፎን በማድነቅ በከተማ ኮሪደር ልማት ስራዎችም እንዲደግሙም ጠይቀዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸውም የቤንች ብሔር በልማትና በአብሮነት የሚያምን ህዝብ ነው ብለዋል።

ተፈጥሮን ጠብቆ ለትውልድ የሚያስተላልፍ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ህዝብ ነውም ብለዋል ።

የቢስት ባር አሮጌውን ዓመት በመሸኘት አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት የበኩር እህል በጋራ የምንቆምበት ለፈጣሪ ምስጋና የምናቀርብበት በዓል ነው ብለዋል።

በቤንች ብሔር የደረሰ እህል ለብቻ መጠቀም እንደነውር የሚቆጠር በመሆኑ ህዝቡ ከወንድምና እህት ጎረቤቶቹ ጋር በጋራ የሚቃመስበት ድንቅ በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል ።

የቤንች ሸኮ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኮይካ ባስተላለፉት መልዕክል የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል “ቢስት ባር”የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የበኩር በዓል ሐይማኖታዊ ይዘት የሌለው የማህበረሰቡ ሁነት ነው በለዋል።

በበዓሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የብሔረሰቦች ምክርቤት የተከበሩ አቶ መቱ አኩ፣ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች፣የአካባቢው ነዋሪዎች ፣የቤንች ነገዶች፣የሸኮ ንጉስ፣የካፋ ንጉስ፣የሸካ ንጉስ ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *