








የአረንጓዴ አሻራን እና የተፋሰስ ልማትን አቀናጅቶ በመተግበር በተፈጥሮ ሀብት ልማት አርዓያነት ያለው ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የ2017 ዓ.ም ሀገራዊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄን በሳይንስ ሙዚየም በይፋ አስጀምረዋል።
በዓይነቱ የመጀመሪያና የንቅናቄ ማስጀመሪያ አካል የሆነ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሲምፖዚየምና ዐውደ ርዕይም ”የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን’’ በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው፥ የግብርናው ዘርፍ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት ከ32 በመቶ በላይ ድርሻ በመሸፈን ለኢኮኖሚው ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል በመሬት መራቆትና በአፈር መሸርሸር ከተጎዱ ሀገራት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሆና መቆየቷን አውስተዋል።
ለአብነትም በደጋማ የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኘው 50 በመቶ መሬት በከፍተኛ መሸርሸር የተጎዳ መሆኑ፣ በሀገሪቱ በየዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን የሚገመት የአፈር ክለት እንደነበርም ገልጸዋል።
ይህም የአፈር ለምነትን በመቀነስ ምርታማነት እንዳይጨምርና ለአየር ንበረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ እንዲሆን ማድረጉን አንስተዋል።
መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ከተፋሰስ ልማት ጋር በማቀናጀት ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የልማት ሥራ መተግበሩን ገልጸዋል።
በዚህም አርዓያነት ያለው ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ለዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና አያያዝ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የፖሊሲ እና የህግ ማእቀፎች ተዘጋጅተው እየተተገበሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ግቦችን ለማሳካት ህዝቡ በየዓመቱ እስከ 60 ቀናት በሚቆይ የነጻ ጉልበት አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
በዚህም የበጋ ወራት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን የማከናወን ባሕልን ማዳበሩን፣ በተለያዩ የግብርና ልማት ዘርፎች ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የደን ሽፋንን በማሳደግ በኩል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፥ አርሶ አደሩ በፍራፍሬና በእንስሳት መኖ ተክሎች ተጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
በሚቀጥሉት 15 ዓመታት በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር የተራቆተ መሬትን ለማገገም የኢትዮጵያ የስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ ውሏል ብለዋል።
በመሆኑም የተፋሰስ ልማትን በማስፋት የአፈር ሀብትን ለሀገር ብልጽግና ለማዋል ሁሉም አካላት በቅንጅት ሊረባረቡ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የዘንድሮው ሀገራዊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ላይ በስፋት በመሳተፍ ማሳካት እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ብትሆንም ባልተገባ አያያዝ ለአካባቢ መራቆትና ለተፈጥሮ አደጋዎች መጋለጥ አጋጥሟታል ብለዋል።
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ተፋሰስን መሠረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራን ማስጀመሩን አንስተዋል።
በተለይም ተፋሰስን የማልማት ሥራ ዋና ባለቤት ህብረተሰቡ መሆኑን በማመን ከፍተኛ ንቅናቄ መፈጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም በየዓመቱ 14 ሚሊዮን ህዝብ በማሳተፍ በተሠራው የተፋሰስ ልማት ተራቁቶ ከነበረው መሬት ውስጥ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታሩ እንዲያገግም መደረጉን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የግብርና ፈንድ ዳይሬክተር ማዊራ ቺቲማ፥ ኢትዮጵያ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሰጠችውን ትኩረት አድንቀዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙና ደን እንዲለብሱ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ልማት አጋርነታችን ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
