የዳዉሮ ብሔር የማንነቱ መገለጫ የሆኑ መንፈሳዊና ባህላዊ ሀብቶች የበለጠ እንዲተዋወቁ የሚያስችል ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ በዳዉሮ ዞን በታርጫ ሂዶታ (አዳሪ) ትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ገለጹ

Spread the love

የትምህርቱ ቤቱ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች የዳዉሮ ባህል ሙዚየም ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ከ9ኛ ተማሪዎች ውስጥ ተማሪ ሳሮን አማኑኤል እንደተናገረችው የቀድሞ አባቶች ሲገለገሉ የነበሩት ቁሳዊ ሀብቶች ተደራጅተው የተቀመጡትን መጎብኘታቸው አስደስቶታል።

ተማሪ አስማማው አባይነህ በበኩሉ እኛ ይህንን የዳዉሮ ባህል ማዕከል በመጎበኘታችን ዕድለኞች ነን ሲል የተናገረ ሲሆን ቀጣይ ሙዚየሙ በተለያዩ የክፍል ደረጃ በሚገኙ ተማሪዎች እንዲጎበኝ ሊደረግ እንደሚገባም ጠይቋል።

ሌላው ተማሪ ተስፋዓለም ታምራት በበኩሉ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆችና የልማቱ ደጋፊዎች የዳዉሮን ባህልና ቅርሶችን በማስተዋወቅ በኩል የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባሉ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

በተለይም በአንዳች ምክንያት ወደ ዞኑ ለሥራ ጉዳይ የሚመጡ እንግዶች የባህላዊ ልብስና ፎጣ ከማበርከት ባለፈ ሙዚየሙንም እንዲጎበኙ ቢደረግ የተሻለ እንደሆነም ነው የተናገረው።

በመጨረሻም ተማሪዎቹ እንደሚሉት በጉብኝቱ ወቅት ሙዚየሙ ጨለማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚታየው ጉድለት በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች እንዲስተካከል ጠይቀዋል።

በዳዉሮ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ውስጥ የሙዚየሙ አስተባባሪና የዕለቱ አስጎብኚ አቶ ላቀው በተላ ለተማሪዎች እንዳብራሩት ዕለት በዕለት የሙዚየሙ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ስለሆነም ከሰኞ እስከ ዓርብ በማናቸውም የሥራ ሰዓት ሙዚየሙ ክፍት መሆኑን አስረድተው እሁድ ከሰዓትም ለሚመጡ ጎብኚዎች አገልግሎት እየተሰጠ እንዳለም ገልጸዋል።

ከመብራት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ከሰሞኑን ከኃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።

ሙዚየም ውስጥ የሚገኙ ቁሳዊ ሀብቶች ጋር ተያይዞ ጽዳታቸውን ለማስጠበቅ በባለሙያዎች በውኃ፣ በጋዝና በቅቤ ወዘተ የሚጸዱ በመሆናቸው ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበው እየተጠባበቁ ስለመሆናቸውም አስረድተዋል።

በሂዶታ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዳዉሮኛ ቋንቋ መምህርት ሰናይት ጦፉ በበኩላቸው በንድፈ ሃሳብ ደረጃና በቃል ደረጃ የሚያውቋቸውን ቁሳዊ ሀብቶችን ተማሪዎቻቸው በተግባር እንዲመለከቱ መቻላቸው ደስታን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በቀጣይም በትምህርት ቤታቸው የሚገኙ ተማሪዎች እንዲጎበኙ የሚያስችል ሥራም እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

ሙዚየሙን ብቻ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ የብሔሩ መገለጫ የሆኑ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶቻቸውን በማስጎበኘት ተማሪዎች እንዲተዋወቁ የሚያስችል ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠሩም ነው የገለጹት።

በመጨረሻም ሙዚየሙ በዚህ መልክ ተደራጅቶ መቀመጡና አስጎብኚው በተገቢው ለተማሪዎቻቸው ስለሰጡት ማብራሪያም ማመስገናቸዉን የዳዉሮ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዘግቧል።

በቅርቡም ይሁን በሩቅ የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን በተቻላቸው አቅም ከማንነታቸው መገለጫ ከሆኑ ቅርሶችና ባህሎች ጋር እንዲተዋወቁ የሚያስችል ሥራ ቢሠራ የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *