



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮና የተጠሪ ተቋማት የ9 ወራት የሴክተር ጉባኤ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ባለፋት 9 ወራት በክልሉ ሠላምን ለማረጋገጥ በቅንጅት በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
አቶ አንድነት ህብረተሰብን በማሳተፍ የጸጥታ ተቋማት በቅንጅት በሰሩት ስራ በሁሉም የክልሉ አከባቢ ሠላምን በማረጋገጥ ለማህበራዊና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል መፈጠር መቻሉን አብራርተዋል።
የብልፅግና ጉዞን ለማሳለጥ ሠላምን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ያሉት አቶ አንድነት የተገኘው ውጤት በየደረጃው ያለው አመራር በሰጠው ትኩረት በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።
የተገኘውን ሠላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ በቀጣይ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅ የገለጹት የቢሮው ኃላፊ የህግ የበላይነትን በሁሉም ረገድ ማረጋገጥ፣ የመረጃ ተደራሽነትና ጥራት ማስፋት፣ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዜዴዎችን ማጎልበት፣ የጸጥታ መዋቅሮች ተልዕኮና ውጤታማነት መፈተሽ እንዲሁም የመፈጸም አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ክልሉ ከጎረቤት የውጪ ሀገር ጋር ድንበር የሚጋራ በመሆኑ በቀጠናው ዘላቂና አስተማማኝ ሠላምና ለማስፈን ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝና በዚህም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ትኩረት በክልሉ መንግሥት መሰጠቱ ተጠቁሟል።
ጉባኤው በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን በማስፋት በሚቀጥሉት 90 ቀናት ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የእርብርብ ማዕከል በማድረግ አጠቃላይ ክልላዊ ሠላምና ልማትን በጽኑ መሠረት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ የክልሉ ፖሊሲ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሸዋኖን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን የመንግሥት ሀላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
መድረኩ ለቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን ከየዞን የሠላምና ጸጥታ መምሪያዎች በሚቀርበው የአፈፃፀም ሪፖርት መነሻ ውይይት እንደሚደረግ ከወጣው መርሀግብር መረዳት ተችሏል።
በዕድገቱ በዛብህ
