ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥል እንደሚገባ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2018 በጀት የግማሽ ዓመት የፓርቲና የመንግስት ተግባራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ እንደገለጹት በኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት አበረታች ውጤቶች መመዝገቡንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የተቻለበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም በመኸር ግብርና፣ በሌማት ትሩፋት፣ በገቢ አሰባሰብ ፣በሥራ ዕድል ፈጠራ፣በቡና ልማት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ተስፋ ሰጪ ዉጤቶች እየታዩ መሆኑን ወ/ሮ ወሰነች በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

ከግብርና ልማት ሥራዎች አንፃር በበልግና በመኸር ግብርና 384 ሺህ 460 ሄክታር መሬት በዋና ዋና አዝርዕት ሰብሎች በመሸፈን 20 ሚሊየን 327 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ተችሏል፡፡

በግብርና ሜካናይዘሽን ከ9 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 14 ሺህ 834 ሄክታር ማልማት መቻሉን ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት ሥራም 147 ሚሊየን ዕንቁላል መመረቱን ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።

ባለፉት 6 ወራት 13 ሺህ ቶን ቡና፣ 18 ሺህ ቶን ቅመማ ቅመም እና 27 ሺህ ቶን የሻይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ወ/ሮ ወሰነች ተናግረዋል፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራትንና ዩኒዬኖችን የማጠናከር እና ወደ ሥራ የማስገባት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 24 ሺህ 210 ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ኃላፊዋ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ተግባራት አንፃር የተለያዩ የመጠባበቂያ እህል በመሰብሰብ 1450 የሚሆኑ አደጋ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በክልሉም 8 የሰንበት ገበያዎች ተከፍተዉ ለነዋሪዎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙ ወ/ሮ ወሰነች አንስተዋል።

ከገቢ ሥራዎች አኳያ በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 06 ቢሊየን ገቢ መሰብሰቡን የገለጹት ወ/ሮ ወሰነች 87 በመቶ የተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *