የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትልቅ ሚና ያለው የሰንበት ገበያ በአመያ ከተማ ተጀመረ።

Spread the love

የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትልቅ ሚና ያለው የሰንበት ገበያ በዛሬው በኮንታ ዞን አመያ ከተማ የዞኑን የከተማ አስተዳደር የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ኡቴ እንደገለፁት በአመያ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለማቅለልና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑንና ለዚሁ ሥራ የሚያግዝ የሰንበት ገበያ መጀመሩን ገልጸዋል።

በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ በሆኑ ምክንያቶች ያጋጠመውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ አንዱ የሰንበት ገበያ ማዕከላትን ማቋቋምና አምራቾችን በቀጥታ ምርቶቻቸው አምጥተው ለሸማቹ ማህበረሰብ ማቅረብ የሚችሉበት በመሆኑ በከተማው 6 ሸዶችን በማስገንባት የተጀመረው ይሄው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በአቅራቢያው በማገናኘት የዋጋ ንረትን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሠራ አቶ ወንድማገኝ ተናግረዋል።

የአመያ ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የከንቲባ ተወካይ አቶ ታምራት ጫንያለው እንደገለፁት የሸማቹን ማህበረሰብ ራሱን ከህገወጥ ነጋዴዎች በማራቅ መንግሥት ያመቻቸውን አጋጣሚ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትልቅ ሚና ያለው ዛሬ የተጀመረው የሰንበት ገበያ ሌሎች የነጋዴ ማህበረሰብንም በማስተባበር ቀጣይነት እንዲኖረው ይደረጋል ማለታቸዉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *