
ኅብረተሰቡ ከወቅታዊ ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ (Hemorrhagic Fever) ራሱን እንዲከላከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አሳስቧል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በመልዕክታቸው፥ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየበት ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አከባቢ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ልዩ ጥንቃቄ ያሻል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ የምዕራብ ኦሞ ዞን እና የካፋ ዞን ጎባ ወረዳ አከባቢዎች በሽታው ከተከሰሰበት አካባቢ ጋር ዘርፈ-ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚ ትስስር ያለበት እንደሆነ ያመለከቱት ኃላፊው፥ በቀጠናው የሚደረጉ ማህበራዊ ግኑኝነቶች በሽታውን ከመከላከል አኳያ በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሽታው፥ በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ አደገኛ ትኩሳትና ደም መፍሰስ የሚያስከትል ሲሆን በበሽታዉ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንኪኪ ሲኖርና በአስተላላፊ ትንኞች በዋናነት የሚተላለፍ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኢብራሂም፥ በሽታው ካለበት ሰው ጋር ከሚደረግ ቀጥተኛ ንኪኪ በተጨማሪ በሽታው በነፍሳት (ትንኝ) ንክሻ የሚተላለፍ መሆኑ የከፋ ያደርገዋል ብለዋል።
በመሆኑም በኅብረተሰብ የጤና ኢኒስቲትዩት ከተዘረዘሩት የመከላከያ መንገዶች በተጨማሪ የአልጋ አጎበርን በተገቢው በመጠቀም በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ኃላፊው ገልጸዋል።
የሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ምልክቶች ከወባ በሽታ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው በመኾኑ ኅብረተሰቡ በተለይም ትኩሳት፣ የሰውነት ጡንቻ መዛል፣ የድካም ስሜት ሲሰማና በአፍንጫ፣ በአፍና በሌሎች የሰዉነት ክፍሎች የደም መፍሰስ ምልክት ሲከሰት ሳይዘናጋ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ እንደሚጠበቅበትም አቶ ኢብራሂም በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
የበሽታው ምልክት የታየበት ሰው ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም መድረስ ካልቻለ በሽታውን ከማስፋፋት በዘለል በሽታው በሰውነት ውስጥ እየጸና በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለሞት የሚዳርግ እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል።
የበሽታው ምልክት በቤተሰብ ውስጥ ሲታይ በቅድሚያ ለሌሎች እንዳይስፋፋ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ኢብራሂም፥ የጤና ባለሙያዎችም ተገቢውን ራስን የመከላከያ መርህ ተከትለው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ምንም እንኳን በክልሉ እስካሁን የበሽታው ምልክት ያልታየ ቢሆንም፤ ክልሉ የበሽታው ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተበት አከባቢ ጋር አዋሳኝ በመሆኑና የጠነከረ የህዝብ ለህዝብ መስተጋብር ያለበት በመሆኑ ጥንቃቄ እንዳይለይ አስገንዝበዋል።
በክልሉ በሽታውን ቀድመው ለመከላከል በክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል የድንገተኛ ጤና ችግር የሚከተታል ማዕከል EOC (Emergency Operation Center) በማጠናከርና የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት ተዘርግተው፣ በንቃት ክትትል እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፥ የበሽታው ቅኝት በየደረጃው በሚገኘው የጤና መዋቅር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በሽታው ከተከሰተበት አከባቢ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ሲኖሩ በቤታቸው እንዲቆዩና ክትትል በማድረግ የበሽታውን ምልክት ሲመለከት በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የጤና ተቋማት ማሳወቅ እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ኢብራሂም በጤና ሚኒስትር እና በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚተላለፉ ወቅታዊ መረጃዎችን በመከተል መተግበር ይገባል ብለዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
