





የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ ቢስት ባር በሲዝ ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የቤንች ብሔር ነው።
የቤንች ብሔር የራሱ የሆኑ ቱባ ባህል ያለው ሲሆን ከእነዚህ ቱባ ባህሎች ውስጥ ደግሞ የ”ቢስት ባር” የዘመን መለወጫ በዓል አንዱ ሲሆን ከሩቅም ከቅርብም ያሉ በጋራ ተሰባስበው የሚያከብሩት ለህጻናትና ለወጣቶች ምክር የሚሰጥበት የመደመር አስተሳሰብ በተግባር የሚገለጽበት በዓል ነው ።
የቢስት ባር የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን በዛሬው ዕለት በሲዝ ከተማ አስተዳደር በፓናል ውይይት ተከብሯል ።
የቢስት ባር ታሪካዊ ዳራው ምን እንደሚመስል በተገቢው ተጠንቶ ለትውልዱ ሊተላፍ በሚችልበትና በዓለም በማይዳሰሱ ቅርስ እንዲመዘገብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ተመራማሪዎች ጥናታዊ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል ።
በውይይቱም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን የ”ቢስት ባር” አከባበር በተጠና መንገድ እንዲከበር ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚህም በተጠና መንገድ መከር ከጀመረ 3 ዓመት የሆነዉ መሆኑንና በተደራጀ መንገድ እየተከበረ መምጣቱን አብራርተዋል ።
የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ “ቢስት ባር ” ከበዓል ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን አቶ ፍቅሬ አማን ገልጸዋል።
በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ በፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት እያቀረቡ ይገኛሉ ሲል ቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።
