ባህልን አልምቶ ተንከባክቦ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ገለጹ።

Spread the love

የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ “ቢስት ባር ” በፓናል ውይይት በሲዝ ከተማ እየተከበረ ነው።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ቢስት ባር የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር የሚያጠናክር በዓል ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

ቢስት ባርን የበለጠ እንዲለማም ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብሮ በማስተሳሰር ማሳደግም ይገባል ብለዋል።

ቢስት ባር ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች የተነሳ ትልቅ የሀገር ሀብት ነው ሲሉም ተናግረዋል ።

የቤንች ብሔር የዘመን አቆጣጠሩን ከጨረቃ ዑደትና ከምርት አሰባሰብ ጋር በማዋሃድ አዲስ ዓመትን ቀምሮ ያከብራል ብለዋልም አቶ ሀብታሙ ።

የቤንች ብሔር በርካታ ቱባ ባህሎች ያሉት ሲሆን እነዚህን ቱባ ባህሎች አጥንቶና አልምቶ ከመጠቀም አንጻር ገና ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ቢስት ባር በተጠና መንገድ መከበር ከጀመረ ወዲህ በተሻለ መልኩ እየተከበረ ይገኛልም ብለዋል።

ወጣቱ ትውልድ ይህንን ባህል የራሱ በማድረግና ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲያደርግም ራሳቸውን ችለው ማክበር መጀመራቸው የሚበረታታ መሆኑን አመላክተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የሼይ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፍሌ ጎበዜ የቢስት ባር ከዘመናት በፊት በማህበረሰቡ ዘንድ ባልተደራጀ መንገድ ሲከበር እንደቆየ ተናግረዋል ።

ጊዜው ደርሶ አሁን ላይ በተደራጀና በተጠና መንገድ ማክበር ከተጀመረ 3 ዓመታትን አስቆጥሯል ብለዋል።

ቢስት ባር አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ፣አሮጌውን ዓመት የምንሸኝበትና የደረሱ እህሎችን በጋራ የምንቀምስበት በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል ።

የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ “ቢስት ባር ” የፌዴራል፣የክልልና የዞን እንዲሁም የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣ወጣቶችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ሲዝ ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ መሆኑን የቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *