





የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ የሲቪል ሰርቪሱን የማስፈጸም አቅም ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያስችል ተመላከተ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010ን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ አካሂዷል።
የአዋጁን ማሻሻል አስፈላጊነት፣ ዓላማ፣ ይዘት፣ ተፈጻሚነትና ሌሎች አጠቃላይ የአዋጁ ድንጋጌዎች ላይ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሕግ ጉዳዮች ዴስክ ኃላፊ መስፍን ረጋሳ ገለፃ አድርገዋል።
የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደርን ለማሻሻል፣ ምርታማነትን ለመጨመርና ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ጉዳዮችን በማስተካከል ለሥራ ሰፊ ጊዜ መስጠት በማስፈለጉ ማሻሻያው መደረጉን ጠቅሰዋል።
አስተያየት የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች አዋጁ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ከማዘመን አንፃር ያለውን ፋይዳ አንስተዋል።
በተመሳሳይ ከሥራ ምዘና፣ የደመወዝ እርከን ማስተካከያ እንዲሁም ልዩ ባህሪያት ያላቸው ተቋማት በአዋጁ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ላይ ጥያቄና አስተያየቶች አንስተዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) በረቂቅ አዋጁ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን በግብዓትነት በመውሰድ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ረቂቅ አዋጁ በብቃት ላይ የተመሠረተ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ፣ ነፃና ገለልተኛ፣ የተገልጋይን እርካታ የሚያሳድግ፣ የሀገር ምጣኔ ኃብት እድገትን የሚያሳልጥ አሠራር ለመዘርጋት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
የሠራተኛውን መብት የሚያስጠብቅ፣ ዘመናዊ አሠራርን የሚዘረጋ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍንና የተሻለ የፈጸሙ የሚበረታቱበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
በሲቪል ሰርቪሱ እየተሰጠ ያለው አገልግሎትና የተቋማት የማስፈጸም አቅም ችግርን ለመፍታትና አሠራርን ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
አዋጁ የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ የተቀረጸ ሳይሆን በኢትዮጵያ በሲቪል ሰርቪሱ የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል ችግር ለመፍታት የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዋጁ መሠረት የመፈጸም አቅምን ለማጠናከር፣ ስታንዳርዳይዜሽንን ለመፍጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ይህ ማለት ግን ተመሳሳይ የደመወዝ፣ ሥርዓትና መዋቅር ተግባራዊ ማድረግ አለመሆኑን አንስተው፤ ይልቁንም ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነትና ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም መገንባት ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነሩ የተለየ ተቋም የሚባል መኖር እንደሌለበት በአዋጁ ላይ በካቢኔ ውይይት ሲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን አስገንዝበዋል።
የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) በውይይት የተነሱ ኃሳቦች ለአዋጁ መዳበር አስተዋጽዖ እንዳላቸው ገልፀዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በሠራተኛ ምዘና፣ በአቅም ግንባታ፣ የሠራተኛውን መብት የሚያስከብር፣ የተገልጋይን እርካታ የሚያመጣ አዋጅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በአዋጁ ላይ ተጨማሪ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች እንደሚያዘጋጅ ሰብሳቢው ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
