ከተቋቋመ በአንድ ወር ውስጥ 8 ሺህ ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ሸኝቷል፦ የቦንጋ ምርት ጥራትና ሴርትፊኬሽን ማዕከል

Spread the love

ቡና ብዙ ተጠቃሚ ካላቸው እና ብዙ ጥቅም ላይ ከሚውሉ መካከል አንዱ ነው፡፡ አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ከሆነ በዓለም ላይ በቀን በጣም ብዙ የሚባል ሲኒ ቡና ተጠቃሚ እንደለው ነው የሚነገረው፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም አሁን አሁን በየቦታው የጀበና ቡና ቤቶች ተከፍተው ይገኛሉ፡፡ ይህም ስራ ዕድል መፍጠሩ አንዱ ነገር ሆኖ ሳለ ከዚህም በተጨማሪ ቡና በሀገር ደረጃ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደለው የሚያሳይ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጀ ቡናን የሚያቀርቡ በርካታ ሀገሮች ቢሆኑም ሀገራችንን ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት የዓለማችንን ቡና አቅርቦት 75 ከመቶ ገደማ የሚሆነውን ይሸፍነሉ፡፡

በተለይም በ2021 እ.ኤ.አ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ለዓለም ገበያ ቡናን በጥራት በማቅረብ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስሟ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡

ኮፊ አረቢካ ቡና መገኛው ሀገራችን ኢትየጵያ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን በዓለም ላይ ተፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን የቡና ተፈላጊነቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ጥራት ባለው የምርመራ ሂደት ማላፉ የተፈላጊነቱን መጠን እንደሚጨምርም ይነጋራል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ጥራት ጉዳይ ሲነሳ የኢትዮጵያ ቡና ምርት ጥራት ምርመራ እና ሴርትፊኬሽን ማዕከል አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የቡና ምርት በመጨመር የአቅራቢ ነጋዴዎች እና የአምራች አርሶአደሮች እንግልት ለመቀነስ  ተሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሴርትፊኬሽን ማዕከል ከዚህ ቀደም ሲል እንደሀገር  ሁለት ብቻ የነበረውን በአሁኑ ሰዓት  የማዕከላቱን ብዛት ወደ ስድስት ከፍ አድርጓል፡፡

ከነዚህም ማዕከላት አንዱ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቦንጋ ምርት ጥራትና ሴርትፊኬሽን ማዕከል መሆኑን የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ያሲን አባግሳ ገልፀዋል፡፡

 የቦንጋ የቡና ምርት ጥራትና ሴርትፊኬሽን ማዕከል የዛሬ አንድ ወር ገዳማ በይፋ ሲራ የጀመረ ሲሆን የተቋቋመበት ዋና ዓላማው ከአከባቢው የሚወጣውን ቡና የምርት ጥራት ደረጃ ማረጋገጥ መሆኑን ኃላፊው ይናጋራሉ፡፡

የውጪ ሚንዛሬ በማስገኘት ጉልህ ሚና የሚጨወታውን የኢዮጵያ ቡና  ጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለውጭ ሀገር ገበያ ለማቅረብ በቡና ምርት ጥራት ምርመራና ሰርትፊኬሽን ማዕከል በኩል ማለፍ የግድ ይለዋል ብለዋል አቶ ያሲን፡፡

ለዚህም  ከቦንጋና አካባቢው እስከ ጋምቤላ ክልል ድረስ የሚመጣውን የቡና ምርት ጥራት ደረጃውን ምስጥራዊነቱ በተጠበቀ መንገድ በማረጋገጥ  ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ የቦንጋ ምርት ጥራትና ሴርትፊኬሽን ማዕከል የምርት ጥራትት ደረጃ የመፈተሽ ስራ እየተሰራ  መሆኑን ነው የማዕከሉ ኃላፊው የገለጹት፡፡

የቦንጋ ምርት ጥራትና ሴርትፊኬሽን ማዕከል መከፈት ከዚህ ቀደም ሲል ጅማ ማዕከል አገልግሎት ለማግኘት ቡና ጭነው እስከ ሁለት ሳምንታት ይቆሙ የነበሩትን መኪናዎች ወደ ሁለት ቀናት ዝቅ የሚያደርግ፣ የላኪና አቅራቢ ነጋዴዎች የመኪና ኪራይና የሾፌር አበል የሚቀንስ እንዲሁም በጊዜ እና ጉልበት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ መሆኑን አቶ ያሲን አብራርተዋል፡፡

ማዕከሉ ከተቋቋመ  አንድ ወር ሆኖታል ያሉት አቶ ያሲን በዚህ ጊዜ ውስጥ   በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን 207 አቅራቢ ነጋዴዎችን በማስተናገድ በቀን ከ10 እስከ 15 መኪና ቡና፤ አንድ ሺህ ቶን የታጠበ እና  ሰባት ሺህ  ያልታጠበ በአጠቃላይ ስምንት ሺህ ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ መሸኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሌለኛው ማዕከሉ በቡና ምርት ጥራት ላይ ብቻ ሳይሆን ከገቢም አንፃር የአገልግሎት እና የከተማ ገቢ እንደሚሰበስብም አንስተዋል፡፡

የአገልግሎት ክፍያ ገቢን በሚመለከት 260 ሺህ ብር ገቢ ተገኝተዋል ያሉት አቶ ያሲን ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ ለብሔራዊ ቡና አቅራቢዎች ማህበርን ለመደጎም ሲባል የሚሰበሰብ  ገቢ መኖሩንና ለዚህም ከ800 ሺህ ብር በላይ  በማዕከሉ መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡

የማዕከሉን አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ 20 ባለሙያዎችን በጊዜያዊነት በመመደብ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የማዕከሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ ከዋናው ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመነጋገር በ2017 በጀት ዓመት ባለሙያዎችን ለመቅጠር ዕቅድ መያዙን አቶ ያሲን አባግሳ  አንስተዋል፡

ከቦንጋ እና አካባቢው ወደ ቦንጋ ምርት ጥራትና ሴርትፊኬሽን ማዕከል በቂ የሆነ ምርት እንደሚቀርብ የገለጹት የማዕከሉ ኃላፊ ከጥራት አንፃር  አሁንም ቢሆን ብዙ መስራት የሚጠይቅ ትልቅ ስራ መኖሩን የሚቀርቡ ቡናዎች ገላጭ ናቸው ብለዋል።

በመጨረሻም ለማዕከሉ የራሱ የሆነ  የመኪና ማቆሚያ ቦታ ባለመኖሩ  ቡና ጭነው የሚመጡ መኪናዎች በአስፓልት ላይ እየቆሙ መሆኑን ገልጸው ይህም ለመኪና እና ለንብረት ደህንነት ምቹ ባለመሆኑ ጉዳዩ የክልሉ መንግሥት እና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ትኩረት ይሻልም ብለዋል አቶ ያሲን አባግሳ፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *