በጤና ተቋማት ፍትሀዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አግልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የለውጥ ትግበራን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የጤናው ስርዓት አዳዲስ ፈጠራዎች መመሪያ፣ ውጤታማ አመራር እና ተጠያቂነት፣ የጤና ተቋማት ልዩ እውቅና አሰጣጥ ፍኖተ ካርታ እና በመጀመሪያ ደረጃ አሀድ ጤና ተቋማት የአሰራር ስርዓት ማነቆዎች ላይ ያተኮረ ሪፎርም ክልላዊ ይፋዊ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በሚዛን አማን ከተማ እያከናወነ ይገኛል።

በመድረኩ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ ከክልሉ ሁሉም መዋቅር የተወጣጡ የጤና አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በክልሉ ሁሉም የጤና ተቋማት የጤና ስርዓት ማነቆ ተኮር ለተቋማዊ ለዉጥ/SBFR/ ተግባራዊ በማድረግ ፍትሀዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አግልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በየደረጃው ያለው የጤና አመራር ተቀናጅተው በመስራት ተገቢውን አግልግሎት ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ቢሮው የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የጤና ሚኒስትር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የጤና ስርዓት ማነቆ ተኮር ለተቋማዊ ለዉጥ/SBFR/ በ2017 በክልሉ ሁሉም የጤና ተቋማት ተግባራዊ እንደሚያደርግም ነው ሃላፊው የገለጹት።

የጤና ስርዓቱ ጠንካራ፣ የማይበገርና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ተቋማዊ ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት ያስገነዘቡት የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ መረጃ መሠረት ያደረገ ውጤታማ የአመራር ስረዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

“በጤናው ዘርፍ ብቃትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአመራር ስረዓት ማስፈን ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ አመራር ይፈጥራል” ያሉት ዶ/ር አየለ ስልጠናው የጤና ተቋማት ራሳቸውን በማሻሻል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፋት ሁለት ዓመት በመላው ሀገሪቱ በተመረጡ ሆስፒታሎች ስተገበር የቆየው የጤና ስርዓት ማነቆ ተኮር ለተቋማዊ ለዉጥ/SBFR/ ውጤታማ በመሆኑ ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት ደረጃዎች ማዳረስ ማስፈለጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

የለውጥ ትግበራው ለማሳለጥ ያስችላል የተባለው ስልጠና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *