ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የኮይሻ- ኦሽካ ዴንቻ ጠጠር መንገድ ግንባታ መርቀው ከፈቱ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በ78 ሚሊዮን ብር ወጭ የተሰራውን የኮይሻ-ኦሽካ ዴንቻ ጠጠር መንገድ ልማት ፕሮጀክት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

44 ኪ.ሜ ርቀት ያለው ጠጠር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ታርጫ ዲስትሪክት ጽ/ቤት የተሰራ ሲሆን ኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ ኮይሻ ከተማን ከኦሽካ ዴንቻ ቀበሌ ጋር የሚያገናኝ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በምረቃ መረሃ ግብሩ የክልሉ መንግስት ከትናንት ያደሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀራረብና በመቀናጀት ችግሮችን እየፈታን እንገኛለን ብለዋል።

ህዝቡ የተሰራውን ምቹ መንገድ በተገቢው በመያዝ የግብርና ምርቶችን በማምረት በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ምርቱን ወደ ገበያ በማውጣት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

ህዝቡ ከግብርና ጎን ለጎን የአከባቢው ሠላምና ፀጥታ መጠበቅ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት አካባቢዉን የተሻለ የኢኮኖሚ ኮርደር

ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሣፒ በወቅቱ የተመረቀው መንገድ ልማት ሁሉም በባለቤትነት ስሜት መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዲዩ መኮንን በክልሉ በ2016 ዓ.ም አጠቃላይ 97ኪ/ሜ የሚሸፍን አራት ጠጠር መንገድ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸው ከ78 ሚሊዮን ወጪ የተደረገበት የኮይሻ-ኦሽካ ዴንቻ መንገድ ከዚህም አንዱ ነው ብለለዋል።

የዞኑ አስተዳደር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለሁሉም ወሳኝ ለሆነው የመንገድ መሠረት ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑን የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ ገልጸዋል።

በአከባቢው የሚገኘው ቡናን ጨምሮ ሌሎች እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ መቀየር እንዲቻል የተጀመሩ መሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብለዋል አቶ ታከለ ተስፉ ።

ለእንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማርቆስ ወንድሙ የክልሉ መንግስት የዘመናት የህዝቦች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምንጭ ሆኖ የቆየው የኮይሻ- ኦሽካ ዴንቻ መንገድ ልማት ፈጣን ምላሽ በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ የክልል፣የዞን፣የወረዳና የአከባቢ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆኑ ለመንገድ ስራ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *