ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በጥናት ለመደገፍ እየተሰራ ነው

Spread the love

ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በጥናት ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በኢንስቲትዩቱ የኤዥያና ፓሲፊክ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጄኔራል አንተነህ ጌታቸው(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ አንዱ ነው ብለዋል።

ይህንን ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር ጎን ለጎን የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ነው ያስረዱት።

አጋርነትን ማስፋት በዲፕሎማሲ መስክ ሊወሰድ የሚገባ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በጥናት ለመደገፍ እየሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ አምራች የሰው ኃይል፣ ግዙፍ የገበያ መዳረሻ፣ የተፈጥሮ ኃብት እንዲሁም የአፍሪካና የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ መዳረሻ መሆኗን አስታውሰዋል።

እነዚህም ኢትዮጵያን በብሪክስ ውስጥ በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅሞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በኤዥያ ፓሲፊክ አካባቢዎች የሚከሰቱ የምጣኔ ኃብት ለውጦችን መሰረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከአካባቢው ሀገራት ጋር ያላትን የምጣኔ ኃብት ዲፕሎማሲን የበለጠ ማጠናከር የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮችም እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በሩሲያ ፌዴሬሽን ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ውስጥ በሚካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በመሳተፍ የባለ ብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኛ አቋም አንጸባርቀዋል።

በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ በነሐሴ 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ባካሄደው15ኛው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያና ኢራን የጥምረቱ አባል እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *