





ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለሀገር ክብር በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው ህዝባዊ ውይይት ተጠናቋል።
በውይይቱም ሰነድ ቀርቦ ተሳታፊዎች ውይይት በማድረግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ከተረጂነት ለመላቀቅ ወደ ስራ መግባት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል ።
አሁን ላይ ከሚያርሰው ይልቅ የሚቀመጠው በዝቷል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ እጅ ለእጅ በመያያዝ ወደ ልማት ልንመለስ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።
ስራ አጥነት ቁጥሩ እጅግ እየተበራከተ በመሆኑ ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ አሁንም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
በየአካባቢው ያሉ የመንገድ መሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊሰሩም ይገባል ብለዋል።
ከድህነትና ከልመና ለመውጣትም ወላጆች ልጆቻቸውን የስራ ባህል ሊያስተምሯቸው ይገባል በማለትም በውይይቱ ሀሳባቸውን አንስተዋል ።
በቋንቋ ልማት ስራዎች የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል ሲሉ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና መ/ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ በሰጡት ማጠቃለያ ህብረተሰቡ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ወደ ልማት በተገቢው መግባት ይኖርበታል ብለዋል።
መሪነት ህዝብን ከችግር ውስጥ ማውጣት ነው ፤ ችግሮችንም ከፊት ሆኖ መጋፈጥ ነው ።በዚህም የተጀመረውን ለውጥ በማጠናከር ሀገራችንንና ህዝባችንን ከተረጂነት አስተሳሰብ ማላቀቅ እንደሚገባም አጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል ።
ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት ተረጂነትን የሚጸየፍ ትውልድ ሊኖር ይገባል ያሉት ዶክተር ሰማ ጥሩነህ የተሻለ ገቢ እንዲኖር የቁጠባ ባህልን ማዳበር ይገባልም ብለዋል።
መንግስት የወባ በሽታን ለመከላከል ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ሰማ በአፈጻጸም ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጣም ጠይቀዋል ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት ችግሮቻችንን ራሰችን በራሳችን መፍታት ይኖርብናል ብለዋል።
ትርፍ በማምረት ከተረጂነት በመላቀቅና የተቸገረውን በመርዳት፣በመደገፍ ያሉንን ልምድ በማዳበር አጠናክረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ማስረሻ በላቸው።
በምግብ ራስ በመቻልና ከልመና ለመላቀቅ ከራስ ባለፈ ለኢኮኖሚ የሚበቃ ምርት ማምረት ይጠበቃልም ብለዋል።
የወባ በሽታ ስርጭት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተስፋፍቶ የሚገኝ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ መድኃኒት ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል ።
ችግሩን ለመቅረፍ ህብረተሰቡ ከራሱ የሚጠበቁ ስራዎችን ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመውጣት ምግቤን ከጓሮዬና የሌማት ትሩፋት ስራዎችንም በሁሉም መስክ ውጤታማ ለማድረግ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ።
ወጣቶችን በስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከ66 የማያንሱ የእርሻ ትራክተሮችን በመግዛት ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ስራ ማስገባቱንም አስታውሰዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በተነሱ አስታያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል።
ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በልማት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተገኘውን ሀብት በመቆጠብ ኢኮኖሚን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ወጣቶችን ወደ ልማት በማስገባት ሁላችንም ኃላፊነታችንን በተገቢው መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር ” በሚል መሪ ቃል በሚዛን አማን ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ ውይይት መድረክ ተጠናቋል።
በታጠቅ አበበ
