ከሰል ማጠቢያና ማበልጸጊያ ፋብሪካ በዳውሮ ዞን፦

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብዙ የማዕድናት ክምችቶች ያሉበት ክልል ነው። ክልሉ በበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገ ነው፡፡ በክልሉ ከፍተኛ ክምችት ያለው የማዕድናት ሀብት ይገኛል፡፡ እንደ ወርቅ ያሉ የከበሩ ማዕድናት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን እና ለመሳሳሉት በግብአትነት ሊውሉ የሚችሉ እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉ በርካታ ማዕድናት በስፋት ይገኛሉ ፡፡ ክልሉ በአሁኑ ወቅት በተለይ በድንጋይ ከሰል ማዕድን ባለቤትነቱ ብቻ ሳይሆን በምርቱም እየታወቀ የመጣ ክልል ሆኗል።
·
የድንጋይ ከሰል በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ማዕድናት ውስጥ አንዱ ነው ፡፡ የድንጋይ ከሰል ጥቁር ቀለም ፣ ጠጣር ፣ ተደራራቢ ፣ በቀላሉ የማይበላሽ መዋቅር ያለው ማዕድን ነው ፡፡ቁሱ እንደ ነዳጅ ስለሚጠቀም የመቀጣጠል ችሎታ ባህሪዎች በጣም ከፍተኛ ነዉ ፡፡

የዳውሮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ነው። ዞኑ ብዙ የተፈጥሮ የተለያዩ ማዕድናት ክምችት ያለበት ነው። ከነዚህም አንዱ የድንጋይ ከሰል በሰፊው ይገኝበታል ። ይህን የድንጋይ ከሰል በማምረት ኢኮኖሚን ከማመንጨት አንጻር ከዚህ በፊት እምብዛም ቢሆንም አሁን አሁን እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

ለዚህም ማሳያው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለማምረት ፈቃድ ለወሰዱ ስምንት ድርጅቶች፣ አስቸኳይ የውጭ ምንዛሬ እንዲቀርብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መወሰኑ ይታወሳል ።

በመሆኑም የድንጋይ ከሰል የማምረት ፈቃድ የተሰጣቸው ስምንት ድርጅቶች አስፈላጊውን የባንክ ፎርማሊቲ አሟልተው ሲመጡ፣ ‹‹የቅድሚያ ቅድሚያ›› እንዲሰጣቸው በመታዘዙ በዘርፉ ፋብሪካውን ግንባታ በማስጀመር ወደ ስራ ከገቡት አንዱ የኢቲ-የማይድን ልማት አክስዮን ማህበር ነው።

ይህ ፋብሪካ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር ግዙፉ የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያና ማጠቢያ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቅቆ በቅርቡ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ይገኛል ።

ፉብሪካዉ በአከባቢው በሰፊዉ ከሚገኘው ክምችት ተቆፍሮ የሚወጣውን የድንጋይ ከሰል በማጠብ የሲምንቶ ፋብሪካዎች ያለባቸውን የድንጋይ ከሰል አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ መንግሥት በየዓመቱ 270 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሲያስገባ መቆየቱን ምንጮች ይጠቁማሉ ።

ፋብሪካው ግንባታ አገራችንን በየዓመቱ የምታወጣውን የመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ወጪ የሚያድን ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት የሆነውን የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በሟሟላት የሲሚንቶ ምርትን የሚያሳድግ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነው።

ችግሩን ለመቅረፍ እየተገነባ ያለው በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያና ማጠቢያ ፋብሪካ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ነው።

ፋብሪካው ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ከመተካትም በላይ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የዳውሮ ዞን ስራ ክህሎት ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ይርጉ ይናገራሉ።

ፋብሪካው እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ ለማትረፍ እንደሚያግዝ አስታወሰው በአከባቢው ኢኮኖሚን ከማነቃቃትም በተጨማሪ ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ከአራት መቶ በላይ ወጣቶች በቋሚና በጊዜያዊ የስራ ዕድል በቅርበት እንዲያገኙ አስችሏል ።

በ2014 ዓ. ም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾና በኢፌዴሪ ማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር በነበሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የመሠረተ ድንጋይ የተጣለና በታርጫ ከተማ አስተዳደር በላላ ገንጂ ቀበሌ በኢቲ-ማዕድን ልማት አክስዮን ማህበር ግንባታው ሲካሄድ የቆየና የሙከራ ጊዜውን አልፎ በሙሉ አቅም ወደ ማምረት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

የፋብሪካው ላለፋት ሁለት ዓመታት ግንባታው ሲካሄድ መቆየቱን የኢትዮ -ማዕድን ልማት አክስዮን ማህበር ተወካይ የሆኑት አቶ ወንድሙ ምትኩ ገልጸው የግንባታው ወጪ ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ መሸፈኑን አንስተዋል ።

የፋብሪካ ግንባታ ዓላማውም ሀገራችን ለሲምንቶና ብረታ ብረት ፋብሪካ ግብዓትነት ከውጭ ሀገር በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ለመተካትና የውጭ ምንዛሬን ወጪ ለማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ጨምሮ አንስተዋል ።

ይህ በኢቲ የማዕድን ልማት ድርጅት የሚገነባውና ግዙፉ ፋብሪካው ተከላ ለማድረግ የተለያዩ ማሽኖችን ከቱርክ ሀገር በማስመጣት ወደ ስራ የተገባው ሲሆን ተከላ የሚያካሂዱት ከፍተኛ ባለሙያዎች ከቱርክ ሀገር በመጡትና ሌሎች ከሀገር ውስጥ በጋራ ሲሰሩ በመቆየታቸው ልምድን ከመቅሰምም እያገዘ ይገኛል ።

ፋብሪካው ከግንባታው በተጨማሪ ለአከባቢው ማህበረሰብ የማህበራዊ አገልግሎትን ከማከናወንና በአከባቢው ልማት ላይ ከመሳተፍ አንጻር በሸባ ዮዮ ቀበሌ በ4.1 ሚሊየን ብር ባለ 4 ክፍል ደረጃውን የጠበቀ ጤና ኬላ ገንብቶ ያስረከበ እንደሆነና በላላ ጋንጂ ቀበሌ ደረጃውን የጠበቀ ባለ 5 ክፍል የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት እና ባለ 4 ክፍል የጤና ኬላ ፣ በታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል የመድኃኒት ፋርማሲ ግንባታ እያካሄደ ከመሆኑም በላይ በዳውሮ ብሔር ባህል ታርክና ምርምር ማዕከል ውስጥ በሚገነባው ባህል አደራሽና ሌሎች የአከባቢው ልማት ላይ የራሱን አሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛል ።

በመሆኑም ከላይ የተገለጸው አጠቃላይ በማህበራዊ አገልግሎት የተሰሩና በመሰራት ላይ የሚገኙ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ድርጅቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ በመስራት ላይ እንደሆነ የድርጅቱ ተወካይ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል ።

ድርጅቱ ከግንባታው ስራ ጎን ለጎን ለግቢው ሠራተኞች የምግብ ፍጆታ የሚዉል እንዲሁም የአከባቢውን ገበያ ለማረጋጋትና ለአርሶ አደሮች ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ የግብርና ስራዎችና የሌማት ትሩፋቶች በተለያዩ የጓሮ አትክልትና የሰብል ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ።

ይህ ፋብሪካው በሙሉ አቅም ወደ ማምረት ሲገባ 450 እስከ 600 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ ወንድሙ የገለጹ ሲሆን የማምረት አቅም 150 ቶን ከሰል በሰዓት የማምረት አቅም መኖሩም እንዲሁም የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን 75 በመቶ የድንጋይ ከሰል ፍላጎት የሚሸፍን በመሆኑ ቀሪ ስራዎች በፍጥነት ተጠናቆ የዘርፉን ችግር ይቀርፋሉ ብለን ተስፋ እያደረግን እንደዚህ ዓይነት ብዙ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት በዘርፉ ሊሰፉና ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *