






በጥናትና ምርምር ስራዎች የግብርና ምርታማነት ማነቆዎችን በመፍታት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በዳሰሳ ጥናት በተለዩ የግብርና ልማት ማነቆዎችና በቀጣይ አቅጣጫ ዙርያ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በምርምር ኢንስቲትዩቱ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታችና ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ኢንስቲትዩቱ የግብርና ልማትና ዕድገትን ለማሳለጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በጥናትና ምርምር የተለዩና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማስፋፋት እንዲሁም የተለያዩ የግብርና አሰራር ዘዴዎችና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ኢንስቲትዩቱ በተሰማራባቸው የምርምር ቀጠናዎች የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
አክለውም ክልሉ ባለው አቅም የምርምር ተቋሙን ማበረታታትና መደገፍ እንዳለበት እንዲሁም ሌሎች መሰል የምርምር ማዕከሎችም በዚሁ መልኩ እየተቋቋሙ የማህበረሰቡን ችግሮች እየፈቱ የሚሄዱበት ሁኔታ ይቀጥላል ብለዋል።
ለአየር ንብረት ተፅዕኖ ተጋላጭ ያልሆኑና ምርታማነትን የሚጨሩ የአካባቢ ዝርያዎችን የመለየትና የማሻሻል ስራ እንዲሁም ቴክኖሎጂን የማለማመድ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የምርምር ኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ ገልጸዋል።
በዕለቱ በክልሉ በተመረጡ ወረዳዎች የተሰሩ አራት የዳሰሳ ጥናቶች በቅደም ተከተል፡- የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም፥ የሰብል ምርምር ስራዎች ጥናት፥ የተፈጥሮ ሀብት ምርምር ስራዎች ጥናት እና የእንስሳት ምርምር ስራዎች ጥናት በሚሉ ርዕሶች በምርምር ኢንስቲትዩቱ አጥኚዎች ለተሳታፊዎች በገለፃ ቀርቦ በውይይት ተጨማሪ ግብዓት ለመሰብሰብ ተችሏል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቀረቡ የጥናት ውጤቶች በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች የግብርና ምርታማነት ማነቆዎችን በመለየት እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ወደተግባር በመግባት ውጤት እንደሚያመጡ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ማስረሻ በላቸው፥ የክልሉ ምክርቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አዲስ ምዕራፍ ዓለሙ፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፥ የምርምር ኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፥ የዞን ግብርና እና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ ኃላፊዎች፥ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የወረዳ አስተባባሪዎች፥ እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በእንዳላማዉ ጌታ
