ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የክልሉን የግብርና ዘርፍ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል መርቀው ከፈቱ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የሰጠው ትኩረት ማሳያ የሆነው የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል ሕንፃ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተመርቀው ለአግልግሎት ክፍት ሆኗል።

የምርምር ተቋሙ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ የክልሉ መንግሥት ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት ለመለወጥ የሰነቀውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ታሪካዊ ምዕራፍ መኾኑም ተመላክቷል።

የዚህ ማዕከል መመረቅ በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደጉም በላይ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዘላቂና ዘመናዊ የግብርና ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስገኘው ጠቀሜታ እጅግ የጎላ መኾኑም ይታመናል።

ተቋሙ በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በቀጥታ ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ በማውረድ ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማመንጨትና ለማላመድ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው።

የህንጻ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ ከ137 ሚሊዮን ብር የውጣበት ሲሆን ማዕከሉ የክልሉን የወደፊት ግብርና በጽኑ የእውቀት መሠረት ላይ የሚገነባና ዘርፉን ወደ ላቀ የምርታማነት ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደኾነም ይታመናል።

በምረቃው ስነስርዓት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *