በክልሉ ኦንኮሰርኪያሰስ፣የተላለፊ ዝሆነና የጊኒ ወርም በሽታዎችን ለማጥፋት በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከካርተር ሴንተር ጋር በመተባበር የተቀናጀና የተጠናከረ የኦንኮሰርኪያሰስ እና የተላላፊ ዝሆኔ እንዲሁም የጊኒ ወርም በሽታዎች ማጥፊያ ፕሮጀክት የአጋር አካላት ውይይት በሚዛን ከተማ አካሂደዋል።

በውይይቱ የኦንኮሰርኪያሲስ፣ተላለፊ ዝሆኔ እንዲሁም የጊኒ ወርም በሽታዎች የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርበው ከተሳታፈዎች አስተያየት ተነስተው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶበታል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የፕሮራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ በውይይት መድረኩ እንደገለጹት፤ ካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ በክልሉ ከተደራጀ ጊዜ ጀምሮ በኦንኮሰርኪያሰስ፣ተላላፊ ዝሆኔ እንዲሁም ጊኒ ወርም በሽታዎችን በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ ለማጥፋት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል በዚህም ባለፉት ጊዜያት በክልሉ 13 ወረዳዎችን ከኦንኮሰርኪያሰስ በሽታ ነፃ ማድረግ መቻሉንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለአምስት ዓመት የሚቆይ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት ትኩረት በሚሹ በሽታዎች ላይ በትኩረት ስራዎችን እየሰራ ስለመሆኑንም አቶ ኃይሌ ዘውዴ ገልጸዋል።

በቀጣይ በተለይም ድንበር ተሻጋር የሆኑ በሽታን ለመከላከል ድንበር ዓቀፍ ግብረ ኃይል ማቋቋም ፣ከበሽታ ነፃ የወጡ አከባቢዎችን እንደገና ማጥራትና በቀሪዎቹ 44 ወረዳዎች ትኩረት ማድረግ፣የሴቶች ልማት ቡድን አደረጃጀት ማጠናከርና መደገፍ እንዲሁም በትራኮማ በሽታ ተጠቂ የሆኑ አከባቢዎችን ተለይተው ወደ ስራ መግባት ይጠበቅብናል ብለዋል ኃላፊው።

የካርተር ሰንተር ኢትዮጵያ ምክትል ኃላፊ አቶ የማነ ቀጄላ እንደሀገር ካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ በአምስት በሽታዎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንዳለና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም ከአምስቱ በሽታዎች ውስጥ በተመረጡ ሶስት በሽታዎች ማለትም ኦንኮስርኪያሰስ፣ተላላፊ ዝሆኔና የጊኒ ወርም በሽታዎችን ለማጥፋት ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የክልሉ ጤና ቢሮ ከካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ትኩረት የሚሹ በሽታዎችን ለማጥፋት እየሰራ ያለው ስራዎች መጠናከር እንደሚገባቸው ገልፀው በቀጣይም በጤና ጥበቃ ከሚሰሩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ልምዶች መስፋት ይገባሉ ብለዋል ።

የመድሃኒት አቅርቦትና አጠቃቀም ፣ጥራት ያለው የመረጃ አያያዝ እንዲሁም ስራዎች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ስራዎችን በየወቅቱ እየተገመገመ በጋራ መስራት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም ሀሳባቸውን ሰጥቷል።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ በክልሉ በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ በጤና ፕሮግራም የሚሰሩ ስራዎች እንዲጠናከርና ስኬታማ እንዲሆን የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *