


የተቋቋመው ምክር ቤት በክልሉ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የቅድመ መከላከል እንዲሁም በተለያየ ምክንያቶች ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ የመስጠት ተግባርን በበላይነት የሚመራ መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሰብሳቢነት የተቋቋመው ምክር ቤቱ ሌሎች የልማት ተቋማትንና የዞን አስተዳዳሪዎችን በውስጡ በአባልነት ያቀፈ ነው።
የዞን መዋቅሮች በራስ አቅም የሚከሰቱ አደጋዎችን የመቋቋም አቋም መፈጠር እንዳለባቸው ያሳሰቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የክልሉ መንግሥት አደጋን በመከላከልና በማቋቋም ረገድ ከኮሚሽኑ ጋር በመቀናጀት መጠነ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በክልሉ አልፎ አልፍ የድርቅ አደጋ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ከአካባቢው ስነምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑ ሰብሎችን በማምረት ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በመቀናጀት የእህል ክምችት ለማድረግ የሚያስችል የማዕከላዊ መጋዘን በቀጣይ እንደሚገነባ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የስራ ባህልን በማዳበር ዜጎች በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲለውጡ በአስተሳሰብ ላይ በስፋት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበው ኮሚሽኑ ክልላዊ የአደጋ ስጋት ስትራቴጂክ እቅድ እንዲያዘጋጅ አሳስበዋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አደጋን በመከላከልና መቀነስ ረገድ እንዲሁም በድህረ አደጋ ለተጎጂዎች ድጋፍ የማቅረብ ስራን በተለያዩ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ለማ መሰለ የገለጹት።
በክልሉ የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን የመከላከልና ዝግጁነት ስራን በህብረተሰብ ተሳትፎ መዘርጋት እንዲሁም ክልላዊ የአደጋ ምላሽ ፈንድ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ነው የተነገረው።
በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች በፕሮግራም ተረጂ የሆኑና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በኮሚሽኑ የተለያያ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝም ኃላፊው አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በተቀመጠው ውሳኔ መሠረት በክልሉ የሚከሰቱ አደጋዎችን የመከላከልና የማቋቋም ስራ ህብረሰብን በማሳተፍ ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉ መንግሥት አደጋ ጊዜ ዝግጁነት ምላሽ ፈንድ ለማቋቋም የሚረዳ የህግ ማዕቀፎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲዘጋጅ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በዕድገቱ በዛብህ
